የዕንባ ጠባቂ ተቋም ታሪካዊ አመጣጥ
ረብዕ, 14 December 2011 13:00

የዕንባ ጠባቂ ተቋም ታሪካዊ አመጣጥ

ዕንባ ጠባቂ ታሪካዊ መሠረቱና አነሳሱ ስዊድን ሀገር ሲሆን የመጀመሪያው የዕንባ ጠባቂ ተቋም የተመሰረተውም በዚህችው ሀገር ምክር ቤት እ.ኤ.አ በ18ዐ9 ዓ.ም. ነው፡፡ በንጉሳዊው አስተዳደርና በዜጐች መካከል ስምምነት ሲጠፋና የአስተዳደር በደሎች ሲፈፀሙ ማረምና መቆጣጠርን ዓላማው አድርጐ ነበር ይህ ተቋም የተመሰረተው፡፡

ስለሆነም የዕንባ ጣበቂ ተቋም ከሶስቱም የመንግሥት አካሎች ገለልተኛ ነገር ግን ተጠሪነቱን ለአንድ የመንግሥት አካል አብዛኛውን ጊዜ ለሕግ አውጪው አካል በማድረግ የመንግሥት ሹማምንት፣ ባለስልጣኖች፣ አስተዳዳሪዎችና ተቀጣሪዎች ሕገ-ወጥ የሆነ፣ ፍትህ የጐደለው አስተዳደራዊ እርምጃና ውሳኔ በሕዝብና በግለሰቦች ላይ የሚያደርሱባቸውን ጉዳቶች ለመከላከልና ለማረም እንዲሁም የችግሮቹን ምንጮች በማጥናት መፍትሔ ለመስጠት የሚሠራ ተቋም ነው፡፡ በግለሰቦችና በማህበራት የሚቀርቡ ቅሬታዎችና አበቤቱታዎችን በማዳመጥ መፍትሄ በቀላሉ እንዲያገኝ የሚያደርግ መንግሥታዊ የዜጐች መብት ጠባቂ ተቋም ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የእንባ ጠባቂ ተቋም ሕጐች፣ የአስተዳደር ደንቦች፣ መመሪያዎችና ውሳኔዎች ህጋዊነታቸውን በመከታተልና በመመርመር ከተቻለ የአስተዳደር ጉድለቶች ጉዳት እንዳያደርሱ መከላከል ካልተቻለ ደግሞ የእርምት እርምጃ እንዲወስድ አስተዳደሩን በማሳወቅና በማሳመን ዜጐችን መታደግ ዋነኛው ተግባሩ ነው፡፡በዚህ መሠረት ይህ ተቋም ዋና ሚናው የማሳመንና የማስታረቅ እንዲሁም ልዩ ፖርት ለምክር ቤቱ የማቅረብ እና በመገናኛ ብዙሃን ስለጉዳዩና ስለጥፋቱ ለሕዝብ በይፋ በማሳወቅ ማጋለጥ ነው፡፡ ስለዚህም ተቋሙ በሕዝብ አስተዳደርና በዜጐች የአገናኝ መድረክነት ሚና የሚጫወትና የመፍትሔ ማመንጫ ተቋም ነው፡፡ በአጭሩ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የአስተዳደር ጉድለቶችን በውይይትና በንግግር በማሳመን እርምት የሚጠይቅ እና የተጐጂ ጠበቃ ሆኖ በምክር ቤትና በሕዝብ ፊት የሚከራከር መንግሥታዊ የሆነ ተቋም ነው፡፡

ዕንባ ጠባቂ ተቋም የሕግ ጉድለቶች፣ አግባብነት የሌላቸው መመሪያዎችና ውሳኔዎች አግባብነት ካላቸው የመንግሥት አካል ጋር በመነጋገር እና ለምክር ቤቱ ሪፖርት በማድረግ በአስተዳደር ጥፋት ምክንያት እንባቸውን ላፈሰሱ ዜጐች መፍትሔ የሚያፈላልግና የሚያስገኝ አካል መሆኑን ለተጠቃሚው ማህበረሰብ በሚገባና በቀላሉ በተለያዩ መንገዶች ማሳወቅ መቻል አለበት፡፡

የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋምን ማቋቋም ለምን አስፈለገ?

በሀገራችን መልካም አስተዳደርን ለማስፈን፣ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበራቸውን ለመከታተል ይቻል ዘንድ የተለያዩ የዴሞክራሲ ተቋሞች ተመሥርተዋል፡፡ ከእነዚህ ተቋማት አንዱ የሆነው የኢፌዲሪ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 55 ንዑስ አንቀጽ 15 መነሻ በማድረግ የተቋቋመ ሲሆን፣ ዋና ተልዕኮውም ሕገ መንግሥታዊ መርሆዎች በትክክል እንዲተገበሩ፣ ግልጽ የሆነ መንግሥታዊ አሠራር እንዲኖር፣ ዜጐች የመብታቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ለማስቻል ነው፡፡

 1. በማቋቋሚያ አዋጁ ቁጥር 211/92 እንደተገለፀው የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በዜጐች ላይ የሚፈፀሙ የአስተዳደር በደሎች የሚወገዱበትንና የሚታረሙበትን መንገድ ለመሻት እንዲሁም የመንግሥት አስፈፃሚ አካላት ሚና በዜጐች የእለት ተእለት ህይወት ጋር ያላቸው ቁርኝት እየተጠናከረ በመምጣቱ ፍትሃዊነት የጐደላቸው ውሳኔዎች እንዳይኖሩ ቢኖሩም በወቅቱ እንዲታረሙ ወይም ጉዳት እንዳያደርሱ እንዲሁም አስተዳደራዊ በደል የደረሰባቸው ዜጐች ተጐድተው እንዳይቀሩ ነው፡፡ ይህም ሲሆን የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ስለህግ አውጪው ሆኖ አስተዳደራዊ በደል እንዳይደርስ በመቆጣጠር እንዲያገለግል የተመሰረተ ነው፡፡
 2. ከዚህ በላይ ያየነው ህግ አውጪው ለምን ተቋሙን እንዳቋቋመ ምክንያቱን ያስቀመጠበትን ሲሆን የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዓላማ የተደነገገው በአዋጁ አንቀጽ 5 ስር የዜጐች መብቶች በአስፈፃሚው አካል መከበራቸውንና የህግ የበላይነት መከበሩን ማረጋገጥ፣ ጥራት፣ ቅልጥፍናና ግልፅነት ያለው የመንግሥት አስተዳደር እንዲመሰረት በማድረግ መልካም አስተዳደርን ማስፈን ነው፡፡ ይህንንም ለማድረግ በአንቀጽ 6 ስር ሰፋ ያለ ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡ የተቋሙ የስልጣን ገደብ ሰፋ ያለ መሆኑን የምንረዳው ይህንን አንቀጽ ከአንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 5 እና አንቀጽ 7 ጋር አዛምደን ስናየው ነው፡፡
 3. ተቋሙ የመንግሥት ተቋማት የሚያወጧቸው አስተዳደራዊ መመሪያዎች፣ የሚሰጧቸው ውሳኔዎችና አሰራራቸው የዜጐችን መብቶችና ህገ-መንግሥቱን፣ ህጐችን /ለምሳሌ አዋጆችንና ደንቦችን፣ የማይቃረኑ መሆናቸውን ማረጋገጥ /አንቀጽ 6 ንዑስ አንቀጽ 1/ ሲሆን ተቋሙ በዚህ ረገድ ያለበት ሃላፊነት ሰፊ ነው፡፡ የአስፈፃሚ አካላት አስተዳደራዊ መመሪያዎች ከመጽደቃቸው በፊት ማየትና ተገቢውን አስተያየት መስጠት፣ እንደ አስፈላጊነቱ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ረቂቅ ህጐችን አዘጋጅቶ ማቅረብን ይጨምራል/አንቀጽ 19 ንዑስ አንቀጽ 2/ሠ//፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የአስፈፃሚው አካል ሥራውን በህግ መሰረት የሚያከናውን መሆኑን ለማረጋገጥና አስተዳደራዊ ጥፋቶች እንዳይፈፀሙ ለመከላከል ቁጥጥር የማድረግ /አንቀጽ 6 ንዑስ አንቀፅ /3/ እንዲሁም የተሻለ የመንግሥት አስተዳደርን ለማስገኘት ነባር ህጐች ወይም መመሪያዎች እንዲሻሻሉ፣ አዲስ ህጐች እንዲወጡ ወይም ፖሊሲዎች እንዲቀየሱ የማሳሰብ ስልጣን ተሰጥቶታል /አንቀፅ 6/፡፡ ይህ ሰፊ ስልጣንና ኃላፊት በሃገሪቱ በአጠቃላይ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ለማድረግ የሚያስችለው ሲሆን የሥራውን ክብደትም የሚያመለክት ነው፡፡ የዚህ እንድምታም መልካም አስተዳደርን በስፋትና ለዘለቄታው ለማስፈን ተቋሙ የእያንዳንዱን የመንግሥት ተቋም አሰራርና ደንብ በጥልቀት መመርመር እንደሚጠበቅበት በአዋጅ ኃላፊት ተሰጥቶቷል፡፡

የተቋሙ፣ ራዕይ ተልዕኮና እሴቶች የተቋሙ ራዕይ

በሚቀጥሉት 17 ዓመታት መልካም የመንግሥት አስተዳደር የሰፈነባትና መረጃ የማግኘት መብት የተከበረባት ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኢትዮጵያ ማየት፤

የተቋሙ ተልዕኮ (Mission)

 • ሕብረተሰቡ ስለመልካም አስተዳደር መርሆዎችና ስለ ሕግ የበላይነት ያለውን ግንዛቤ ማሳደግ፤
 • መንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና በመንግሥት ልማታዊ ድርጅቶች የሚፈፀም አስተዳደራዊ በደልን አስመልክቶ የሚቀርብ ቅሬታን ለመፍታት ተቋማቱ ስልት እንዲቀይስ ማበረታታትና ማገዝ፤
 • አስተዳደራዊ በደልን አስመልክቶ የሚቀርብ ቅሬታን በአግባቡ በመቀበልና በመመርመር መፍትሔ መሻት፤
 • ጥናትና ምርምርን መሠረት በማድረግ አስተዳደራዊ በደል በሚታረምበት /በሚቀረፍበት/ ስልት ላይ ሃሣብ ማቅረብ፤

የተቋሙ እሴቶች (volues)

 • ገለልተኝነት
 • ለማዳላት
 • እኩልነትና ፍትሃዊነት
 • ቀልጣፋና ለሕዝብ ቅርብ መሆን ቅንነትና ለሕዝብ ጥያቄ ተገቢውን መልስ መስጠት
 • ፖሊሲና የኘሮግራም ግልጽነት
 • ሚስጢር ጠባቂነት
 • ሕዝብ ተጠያቂ መሆን
 • ባለሙያና በቡድን ሥራን መሥራት
 • በሕግ የበላይነትን፣ ዴሞክራሲያዊ ሂደትንና መልካም አስተዳደርን ማክበርና ማስከበር፤

የተቋሙ ሥልጣንና ተግባራት

የኢትየጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋምን ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 211/1992 እና የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነትን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 590/2000 ሰፊ ስልጣንና ተግባር ተሰጥቶታል፡፡

በማቋቋሚያ አዋጁ አንቀጽ 5 እንደተደነገገው የኢፌዲሪ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዓላማ በሕግ የተደነገጉ የዜጎች መብቶችና ጥቅሞች በአስፈጻሚው አካል መከበራቸውን በማረጋገጥ የሕግ የበላይነትን መሰረት ያደረገ ጥራት፤ ቅልጥፍና እና ግልጽነት ያለው መልካም የመንግስት አስተዳደር እንዲሰፍን ማድረግ ነው፡፡ ተቋሙ የተቋቋመበትን ዓላማ ለማስፈጸም ይችል ዘንድ በማቋቋሚያ አዋጁ አንቀጽ 6 መሠረት የሚከተሉት ሥልጣንና ተግባራት ተሰጥተውታል፡፡

 • አስፈፃሚ አካላት የሚያወጧቸው አስተዳደራዊ መመሪያዎች፣ የሚሰጧቸው ውሣኔዎችና አሰራሮቻቸው የዜጎችን ህገ-መንግሥታዊ መብቶችንና ህጎችን የማይቃረኑ መሆናቸውን መቆጣጠር፣
 • አስተዳደራዊ ጥፋትን አስመልክቶ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን የመቀበልና የመመርመር፣
 • አስፈፃሚው አካል ሥራውን በህግ መሰረት የሚያከናውን መሆኑን ለማረጋገጥና አስተዳደራዊ ጥፋቶች እንዳይፈጸሙ ለመከላከል ቁጥጥር የማድረግ፣
 • አስፈፃሚው አካል ሥራውን በህግ መሰረት የሚያከናውን መሆኑን ለማረጋገጥና አስተዳደራዊ ጥፋቶች እንዳይፈጸሙ ለመከላከል ቁጥጥር የማድረግ፣
 • አስተዳደራዊ ጥፋት መፈጸሙን ያመነበት ከሆነ የመፍትሄ ሃሣብ የመሻት፣
 • አስተዳደራዊ ጥፋቶች የሚሻሻሉበትን ሁኔታ የማጥናትና ሃሣብ የማቅረብ፣
 • የተሻለ የመንግስት አስተዳደርን ለማስገኘት ነባር ህጎች ወይም አሰራሮች ወይም መመሪያዎች እንዲሻሻሉ፣አዳዲስ ህጎች እንዲወጡ ወይም ፖሊሲዎች እንዲቀየሱ የማሳሰብ፣
 • ከዓላማው ጋር የሚጣጣሙ ሌሎች ተግባሮችን የማከናወን፣

ሲሆኑ ተቋሙ በማቋቋሚያ አዋጁ ከተሰጡት ሥልጣንና ተግባራት በተጨማሪ የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነትን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 590/2000 መሠረት ከመንግስታዊ አካላት መረጃ ጠይቆ የማግኘትና እና የማስተላለፍ መብት ጋር በተያያዘ መልኩ ሰፊ ተግባርና እና ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 11 እንደተደነገገው የዜጎች መረጃ የማግኘት መብት በሕግ መረጋገጡ አንዱ አላማ የመንግስትን አሠራር ግልጽነት፣ ተጠያቂነት እና ውጤታማነት የሰፈነበት በማድረግ መልካም አስተዳደርን ማጠናከር ነው፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 12 እንደተደነገገው ማንኛውም ሰው ከማንኛውም መንግስታዊ አካል መረጃን የመጠየቅ፣ የማግኘት እና የማስተላለፍ መብት አለው፡፡ ተቋሙም ይህ መብት ተፈፃሚ እንዲሆን የሚከተሉት ኃላፊነቶች ተሰጥቶታል፡፡

 • የመረጃ ነፃነት ሕግን ለመተግበር የሚያግዙ የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎችን የማዘጋጀት፣
 • የመረጃ ነፃነት ሕግን ተግባራዊ ለማድረግ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ልዩ ልዩ የማብራሪያ ማኑዋሎችን የማዘጋጀትና የማስተዋወቅ፣
 • የመረጃ መጠየቂያ ፎርማቶችን የማዘጋጀትና የማሰራጨት፣
 • በመረጃ ክልከላ ላይ ይግባኝ ሲቀርብ በሕግ በተወሰነው ጊዜ ውስጥ መርምሮ ውሣኔ የመስጠት፣
 • የመረጃ ነፃነት ወጥነት ባለው መልኩ እንዲፈጸም ለመንግስት አካላት ማንዋልና መመሪያ የማዘጋጀት፣ የመረጃ ነፃነት አተገባበርን መከታተልና ለተፈፃሚነቱ አስፈላጊውን ድጋፍ የማድረግ፣
 • ለህዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች የሚሰጡ ስልጠናዎችን የማዘጋጀት ወይም የማገዝ፣
 • ስለመረጃ ነፃነት አፈፃፀም አጠቃላይ ሁኔታ ከመንግስት አካላት ዓመታዊ ሪፖርት በመሰብሰብ ለተወካዮች ምክር ቤት የተጠቃለለ ሪፖርት የማቅረብ፣
 • መረጃ አትሞ ማሰራጨትን በተመለከተ ግልጽ የአሰራር መመሪያ አዘጋጅቶ በመንግስት አካላት ተቋማት እንዲተገበር የማድረግ፣
 • የመረጃ ነፃነትን በመተግበር ሒደት ካጋጠሙ ተሞክሮዎችና ችግሮች በመነሳት ለተሻለ አፈፃፀም የሚያበቃ የውሳኔ ሐሳብ አዘጋጅቶ የማቅረብና ሥራ ላይ የማዋል፣
 • ከመረጃ ማግኘት መብት ጋር ተያይዞ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ለማስተናገድ የሚያስችል ሥርዓት የመዘርጋት፣
 • ለመረጃ ነፃነት አፈፃፀም የሚያስፈልጉ ሌሎች ተግባራትን የማከናወን ስልጣንና ኃላፊነት አለው፡፡
መጨረሻ የተሻሻለው በ ማክሰኞ, 08 May 2012 08:59