የዋና እምባ ጠባቂው መልክት
ማክሰኞ, 20 December 2011 07:23

ክብርት ወ/ሮ ፎዚያ አሚን በሚኒስትር ማዕረግ ዋና ዕንባ ጠባቂ

" የኢፌዴሪ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዜጐችን የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚ ለማድረግ ግልጽነት ቀልጣፋና ጥራት ያለው የመንግሥት አስተዳደር እንዲሰፍን የማድረግ ራዕይ ያለው ተቋም ነው፡፡ተቋሙ በአገራችን የመልካም አስተዳደር ባህል እንዲዳብር እና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና በልማት ድርጅቶች የሚታዩ የአስተዳደር በደሎች እንዲወገዱ ከማድረግ አኳያ በእነዚህ ተቋማትና በዜጐች መካከል የሚነሱ ቅሬታዎችን በአግባቡ ተቀብሎ በመመርመር የመፍትሔ ሃሣቦችን ያቀርባል፡፡በተጨማሪም ለአስተዳደር በደሎች መነሻ የሚሆኑ የሕግ ክፍቶችን በማጥናት እንዲሻሻሉና የእርምት እርምጃዎች እንዲወሰዱ በማሳሰብ የመልካም አስተዳደር ግንባታ ሂደት እንዲጠናከር የበኩሉን ጥረት ያደርጋል፡፡የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የተሰጠውን ይህንን ግዙፍ ኃላፊነት ብቻውን የሚወጣው ባለመሆኑ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ይጠይቃል፡፡ በዚህ መሠረት ሕብረተሰቡ ስለመልካም አስተዳደር መርሆችና ስለሕግ የበላይነት ያለውን ግንዛቤ ማሳደግ የቅድሚያ ትኩረት የሚሰጠው ተግባር ሆኗል፡፡

ይህንን ተግባርና ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ቀልጣፋና ውጤታማ የኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ ሊኖረው እንደሚገባ ይታወቃል፡፡ ከሕብረተሰቡ መረጃዎችን የሚቀበልባቸውና መልሶም ለሕብረተሰቡ አስፈላጊ መረጃዎችን የሚያሰራጭባቸው ልዩ ልዩ ስልቶችን መቀየስ አስፈላጊ በመሆኑ የዚህ ድረ-ገጽ መከፈት እንደ አንድ አማራጭ መንገድ የሚታይ ይሆናል፡፡ የድረ-ገጹ መከፈት በአገራችን የመልካም አስተዳደር መርሆችንና ሌሎች መረጃዎችን ለማሰራጨት ብርቱ እገዛ ይኖረዋል፡፡

በተጨማሪም የሁለትዮሽ የመረጃ ልውውጥ መድረክ በመሆን ምቹ ሁኔታዎችን ከመፍጠሩም ባሻገር በተቋሙ የስልጣን ክልል ውስጥ በሚወድቁ ጉዳዮች ዙሪያ ለዜጐች አጠቃላይ የማማከርና የሙያ ድጋፎች ለማድረግ በመሣሪያነት ያገለግላል፡፡ይህ ድረ - ገጽ ሕብረተሰቡ ከተቋሙ ጋር የሚገናኝበት አንድ ተጨማሪ የመገናኛ ዘዴ ከመሆኑም በላይ በቀላሉ ቅሬታዎችን ወደ ተቋሙ ለመላክ የሚያስችል እድል በመሆኑ ዜጐች በሰፊው ይጠቀሙበታል የሚል እምነት አለን፡፡ "

መጨረሻ የተሻሻለው በ ማክሰኞ, 17 April 2012 08:43