ዘጋቢ ፅሁፍ
‹አንድ እንጨት . . .፣ አንድ ሰው . . .
አርብ, 25 April 2014 10:27

ይህን ሰማሁ፤ ሰውየው ለባለቤቱ ‹ዝናውን› ሲተርክላት- ንግዱ እንደተጧጧፈለት፣ ሸቀጡ ካምሳዮቹ ነጋዴዎች ይበልጥ እንደተወደደለት፣ የደንበኞቹ ቁጥር እንደጨመረ፣ ገበያው እንደደራ፣ ባጭር ጊዜ አምሳዮቹን ከጫማው በታች እንደሚያንበረክካቸው፡፡ ባለቤቱ- አፏን ከፍታ፣ እግሮቿን አንስታ እየዘለለች በደስታና ባድናቆት አሽካካች- አምሳዮቿ የነጋዴ ሚስቶች በቅናት አንጀታቸው ድብን፣ ቆሽታቸው እርር፣ ጨጓራቸው ቅጥል፣ ሽንፍላቸው ላጥ፣ ወሽመጣቸው ብጥስ፣ ቅስማቸው ስብር፣ አንገታቸው ድፍት ሲል በዓይነ ህሊናዋ እየታያት በሀሳቧ ክንፍ አውጥታ በረረች፡፡ ልጅ- ካባቱ ትረካ ‹ዝናውን› ሰማ፤ ከናቱ ፍንክንክታ ደስታዋን አየ፡፡ ንፁኋ ትንሿ ልቡ ያላንዳች ጥርጣሬ አመነቻቸው፤ ነጭ ወረቀት አእምሮውም መዘገበው፡፡ ካባቱ ‹ዝና› ግማሹ፣ ከናቱ ጮቤም እኩሌታው የሷ መሆኑን የገመተችው ነፍሱ በሀሴት ተሞላች፡፡

በማግስቱ- ላምሳዮቹ ተማሪዎች የቤታቸውን ‹ዝና› እንደወረደ ተረከላቸው፡፡ ተቀባበሉት፡፡ በመላ ተማሪው መሀል ናኘ፡፡ ከት/ቤት ት/ቤት ተሸጋገረ፡፡ እንደ ችቦ እየተቀጣጠለ፣ እንደ ሰደድ እሳት እየተዛመተ የወላጆችንና የጎረቤቶቻቸውን ደጃፍ አንኳኳ፤ የነጋዴዎቹ ደጃፍ ላይ እንደ መብረቅ እያጓራ በወደቀ ጊዜ ግን እንደ ዱብ-ዕዳ ወረደባቸው፡፡ አሁን የምር ከጫማው በታች አንበረከካቸው - ንግዱ ተጧጧፈለት፣ ሸቀጡ ይበልጥ ተወደደለት፣ የደንበኞቹ ቁጥር ጨመረ፣ ገበያው ደራ - ተሳካለት፡፡

ነጋዴውና ባለቤቱ ልጃቸው ፊት የተጨዋወቱት ጨዋታ እውነትነት ባይኖረውም ልጃቸው ግን በእምነት ተቀብሎ ለተማሪ ጓደኞቹ እንደሚያወራውና አንዴ ት/ቤት ውስጥ ከተሰማ ማህበረሰቡ ዘንድ ይደርሳል የሚል እምነት አሳድረው ነበር፡፡ ይህ የሚያሳየው፣ መረጃ ትክክለኛም ይሁን የተሳሳተ፣ ጠቃሚም ይሁን ጎጂ፣ አስተማሪም ይሁን ቀስቃሽ ወደ ማህበረሰቡ ለማድረስ ት/ቤቶች ትልቅ ሚና እንደሚጫወቱ ነው፡፡ ለተሳሳተ፣ ለጎጂና ላላስፈላጊ ቅስቀሳ ት/ቤቶችን መጠቀም በስነ ምግባርም ሆነ በሞራል የማይጠቅምና ከርካሽ ፍላጎት ያለፈ ማህበረሰባዊ ፋይዳ የማይሰጥ የመሆኑን ያህል ለትክክለኛ፣ ለጠቃሚና አስተማሪ ለሆነ ምግባር መጠቀሙ ደግሞ የዛኑ ያህል ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ ይህንኑ በመገንዘብም የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ከት/ቤቶች ጋር አፍ ለአፍ ገጥመው ወግ ከጀመሩ ዓመታት አስቆጥረዋል፡፡ ወጋቸው የሚያጠነጥነውም ለዜጎች ጥቅምና ፍላጎት፣ ለሀገር ዕድገትና ብልጽግና፣ ለዲሞክራሲያዊ ባህል ማበብና መዳበር፣ ለመልካም አስተዳደር መስፈንና መረጋገጥ፣ ለመረጃ ነፃነት መተግበርና ዕውን መሆን ፋይዳ በሚሰጡ ምግባሮች ዙሪያ ነው፡፡ እስቲ የወዳጅነታቸውን ልክ አብረን እንቃኝ፡፡

ð ð ð

ት/ቤቶች የመረጃ ገበያ ናቸው፡፡ እዚያ፣ መረጃ ይገበያል፡፡ መረጃ ይሰጣል፣ መረጃ ይወሰዳል፡፡ እዚያ የመረጃ ስስት የለም፤ ሰጪው ሥፍር አድርጎ ይሰጣል፣ ተቀባዩ ዝግን አድርጎ ይወስዳል፤ ይጨማምርለታል፣ ይደጋግምለታል - ለሱም እስኪበቃው፣ ለሌላውም እስኪተርፈው ድረስ፣ እሱም እንዲያካፍል፡፡ እዚያ፣ ሰጭና ተቀባይ መረጃ ሲሰጣጡ፣ ሲከፋፈሉ፣ ሲቀባበሉና ሲለዋወጡ፣ ‹ይዞህ ይደግ፣ ይመንደግ፣ የምትለወጥበት፣ ሀገርህን የምትጠቅምበት ይሁን› ሲባባሉ ይታያል፡፡

ት/ቤቶች የመረጃ ሙዚየም ናቸው፡፡ እዚያ፣ መረጃ ይሰበሰባል፣ መረጃ ይከማቻል፣ መረጃ ይጎበኛል፡፡ መረጃ በየዘርፉ የጎብኚውን ቀልብ በሚገዛና በሚያስደምም፣ ልቡንም በሚማርክና በሚያስጎመጅ መልኩ ተሰድሮና ተሰትሮ ይታያል፡፡ እዚያ፣ ጎብኚው አቅሉ መረጃ ጠግቦ፣ ልቡ በመረጃ በርቶ፣ መንፈሱ በመረጃ ይሞላል፡፡ እዚያ፣ ጎብኚው አሮጌው ማንነቱ ተገርዞ፣ ሸለፈቱ ተቀብሮ እንደ እባብ ቆዳ ተገልፍፎ ባዲስ ማንነት ይታነፃል፡፡

ት/ቤቶች የመረጃ ጅረት ናቸው፡፡ እዚያ፣ መረጃ ከመምህሩ የአእምሮ ጓዳ እየመነጨ፣ ከመጻህፍት ገላ እየተጨመቀ የድንቁርና ቆንጥሩን ደምስሶ፣ ሸለቆና ሰርጡን አቋርጦ፣ ጋራና ሸንተረሩን ዞሮ፣ በገደሉ ቁልቁል እየተወረወረ፣ በተማሪው ተቀባብሎ በየቤቱ፣ በየጎረቤቱ፣ በየቀየው፣ በየማህበረሰቡ እየተንፎለፎለ ከዘላለም የዕውቀት ምንጭ ውሀ የተጠማውን ያጠጣል፤ የጠጣውን ያረካል፤ የረካውን . . .! ት/ቤቶች ትልቁ የመረጃ ቋት በመሆን ለዓለም ዕውቀት ያቋድሳሉ፣ ዕውቀት ይመግባሉ፣ በዕውቀታቸው ይሞላሉ፣ በዕውቀታቸው ይዋጃሉ፡፡ የመረጃ ድርና ማግ እየሸመኑ፣ የመረጃ ፈትል በመፍተል ዓለምን ሀር በመሰለ፣ እንደ ፀሐይ ጮራ በሚያበራ፣ እንደ ማለዳ ፀሐይ በሚፈነጥቅ፣ እንደ ጨረቃ በሚያደምቅ፣ እንደ ክዋክብት በሚያንቆጠቁጥ የመረጃ ኩታ ያለብሳሉ፡፡ ዓለምን ባንድ ቋንቋ ያናግራሉ፣ ባንድ ባህል ያኖራሉ፣ ባንድ አመለካከት ይቀርጻሉ፣ ባንድ እምነት ያፀናሉ፡፡ ት/ቤቶች በመረጃ ኃይል፣ የቀጨጨ አእምሮ ያሳድጋሉ፣ በአመጽ የደነደነ ጡንቻን ያሰክናሉ፡፡

ልጆች በባህሪያቸው የታላላቆቻቸውን ዱካ መከተል፣ ታላላቆቻቸው የሚያደርጉትን ማድረግ፣ የሚናገሩትን አስመስለው መናገር ይፈልጋሉ፣ ይጓጓሉ፣ ይናፍቃሉ፡፡ በታላላቆቻቸው ላይ ታላቅ እምነት አላቸው፡፡ ደግም ይሁን ክፉ በታላቅ የእምነት ጽናት፣ ያላንዳች ጥርጣሬ ይወስዳሉ፡፡ በልጆች ህሊና ታላላቆች የማይሳሳቱ፣ የማይዋሹ፣ የማያቅታቸው ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ ወላጆቻቸው፣ መምህራናቸውና ሌሎች በማህበረሰቡ ውስጥ ከበሬታ ያላቸው ግለሰቦች ፍጹም ናቸው በልጆች ዓይን፡፡ ስለዚህ ልጆች የነዚህን ግለሰቦች ድርጊትና ንግግር ሳይነቅሱና ሳይኩሉ፣ እንደወረደ ለማድረግና ለተማሪ ጓደኞቻቸው ለመናገር ይወዳሉ፣ ይጥራሉ፣ ይሞክራሉ፣ ያደርጋሉም፡፡ ተማሪዎች ለወላጆቻቸው ያጋራሉ፡፡ በስተመጨረሻ መረጃው የማህበረሰቡ አካል ይሆናል፡፡

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 55 ንዑስ አንቀጽ 15 መሠረት በአዋጅ ቁጥር 211/1992 የተቋቋመ ተቋም ነው፡፡ ዓላማውም በህግ የተደነገጉ የዜጎች መብቶችና ጥቅሞች በአስፈጻሚ አካላት መከበራቸውን በማረጋገጥ የህግ የበላይነትን መሠረት ያደረገ ጥራት ቅልጥፍናና ግልጽነት ያለው መልካም የመንግሥት አስተዳደር እንዲሰፍን ለማድረግ ነው፡፡ ተቋሙ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላትና ባለሥልጣናት በሚሰጡት ፍትሀዊነት የጎደለው አስተዳደራዊ እርምጃና ውሳኔ ሳቢያ በህዝብና በግለሰቦች ላይ አስተዳደራዊ በደል ማድረስ አለማድረሳቸውን በማጣራት እንዲታረሙ የምርመራ ሥራ ያከናውናል፤ አቤቱታዎች/ቅሬታዎችን ተቀብሎ በደል መፈጸሙን ሲያረጋግጥ የመፍትሄ ሀሳብ ያቀርባል፤ በደል መፈጸሙን ጥርጣሬ በሚኖረው ወቅትም በራስ ተነሳሽነት ምርመራ ያካሄዳል፣ ጥናት ያደርጋል፣ ድጋፍ ይሰጣል፡፡

ተቋሙ እንደማንኛውም የመንግሥት መ/ቤት ተቋቋመለትን ዓላማ ለማስፈጸም፣ ከዳር ለማድረስና ዜጎችን ለማገልገል ደፋ ቀና እያለ መሆኑ አሌ የማይባል ሀቅ ነው፡፡ ይሁንና ዓላማውን አስፈጸመ፣ ተሳካለት የሚባለው ስለ ዓላማው የተገነዘበ ማህበረሰብ መፍጠር ሲችል እንደመሆኑ ተደራሽነቱን ለማስፋት የተለያዩ የሚዲያ አግባቦችን በመጠቀም ህብረተሰቡ ስለ ተቋሙ ግንዛቤው እንዲጨምርና ግዴታውን ተረድቶ በመብቱም እንዲጠቀም ማድረግ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም የተለያዩ መድረኮችን፣ የህትመት ውጤቶችን፣ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን፣ ድረ ገጾችን፣ እንዲሁም የዚህ ጽሁፍ ዋነኛ አጀንዳ የሆነውን የት/ቤቶች ሚዲያን በመጠቀም ህብረተሰቡን ለመድረስ እየታተረ ይገኛል፡፡

ተቋሙ ት/ቤቶች መረጃን ወደ ማህበረሰቡ በፍጥነት ለማስተላለፍ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወቱ የገባው ዘግይቶ አልነበረም፤ ገና ሥራውን ሲጀምር ዓይኑን ጥሎባቸው ነበር፡፡ በመሆኑም በ1997 ዓ.ም. ሥራውን በይፋ ከጀመረበት ወቅት አንስቶ ከት/ቤት ሚዲያ ጋር በርካታ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ በድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር፣ ሀዋሳ፣ ሐረር፣ አዳማ ጂጂጋ እና ሌሎች ዘጠኝ በሚሆኑ የክልል ከተሞች ከሚገኙ የት/ቤት ሚዲያ ጋር ሰፊ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡ በመሆኑም፣ ስለ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ (Ombudsman) ጽንሰ ሀሳብ ምንነት፣ ስለ ዕንባ ጠባቂ ተቋማት አመሰራረት ዓላማና ፋይዳ በዓለም፣ ስለ ኢፌዲሪ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አመሰራረት፣ ዓላማ፣ ሥልጣንና ተግባር እንዲሁም ተቋሙ ስላከናወናቸው እንቅስቃሴዎች የት/ቢሮ ኃላፊዎች፣ የየት/ቤት ርዕሳነ መምህራን፣ የሲቪክ መምህራን፣ ቡድን መሪዎች፣ የት/ቤት ሚዲያ አስተባባሪዎችና አባል ተማሪዎች ሥልጠና ተሰጥቷቸዋል፡፡ እንዲሁም፣ ስለ ተቋሙ የሥራ መመሪያዎችና ደንቦች፣ ስለ አቤቱታ/ቅሬታ አሰማምና አቤቱታ ቅበላ ሥርዓት፣ ስለ ምርመራ ሂደትና መፍትሄ አሰጣጥ ግንዛቤ እንዲጨብጡ ተደርጓል፡፡ ከህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን የሥራ ክፍል በተገኘው መረጃ መሠረት፣ በ210 ት/ቤቶች የሚገኙ 3,150,000 የሚሆኑ ተማሪዎች በት/ቤት ሚዲያ አማካኝነት ግንዛቤ ያገኙ ሲሆን የጨበጡትንም ዕውቀት ለመላው የየት/ቤቱ ማህበረሰብ እንዲያስተጋቡ፣ የየት/ቤቱ ማህበረሰብም ለሰፊው ህብረተሰብ እንዲያሰማ ከማድረግ አንጻር በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡

ይህንኑ በማስቀጠልም በተለያዩ የክልል ከተሞች ለሚገኙና የት/ቤት ሚዲያ ላላቸው ት/ቤቶች መሰል የግንዛቤ ሥራዎች በስፋት እየተሰጡ ይገኛሉ፡፡ እንቅስቃሴው አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ በተለያዩ የክልል ከተሞች የሚገኙ በርካታ ት/ቤቶች ወር-ተራቸውን እየጠበቁ ይገኛሉ፡፡ ተቋሙ አሁንም ‹ማነው ባለሳምንት?› እያለ በየበራቸው ላይ ቆሞ ያንኳኳል፣ እጅ ለእጅ ተያይዘን ዓላማችንን እናሳካ፣ ግባችን ላይ እንድረስ፣ ህልማችንን ዕውን እናድርግ፣ ራዕያችንን እንይ ይላል፡፡ ‹ድር ቢያብር፣ እንበሳ ያሥር›፣ ‹ካንድ ብርቱ፣ ሁለት መዳኒቱ›፣ ‹አንድ እጅ ብቻውን አያጨበጭብም›፣ ‹አንድ እንጨት አይነድ፣ አንድ ሰው አይፈርድ›፤ ተቋሙ በቅርቡም ከሌሎች የክልል ከተሞች የት/ቤት ማህበረሰብ ጋር አዲስ ወግ ይኖረዋል፡፡ ያድርሰን፣ አሜን!

መጨረሻ የተሻሻለው በ አርብ, 31 October 2014 08:42
 
የብሶተኛው ጩኸትና የመርማሪው ጆሮ
ረብዕ, 26 March 2014 06:46

 

ማን ይፈትሽ- መርማሪው፣

ማን ይተርክ- ዘጋቢው

እነሆ፣ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ አንድ በቅርብ የማውቃቸው ቤተሰብ አባል በመኪና አደጋ ጉዳት ይደርስባቸውና ለአስቸኳይ የህክምና እርዳታ ወደ አንድ የጤና ተቋም ተወሰዱ፡፡ የመጀመሪያ የህክምና እርዳታ ከተደረገላቸው በኋላ ክፉኛ የተጎዳው እግራቸው ለቀጣይ ህክምና በጄሶ ታጀለ፡፡ ይሁንና ግለሰቡ ለቀጣይ ህክምና የሚሆን ጥሪት የሌላቸው ሆነና እግራቸው ‹በስብሶ› በስቃይ እየማቀቁ ‹ከመሞት› ‹ተቆርጦም› ቢሆን ‹መሰንበት› ይሻላል ብለው ቀሪ ዕድሜያቸውን የጤና ተቋሙን በጥበቃ ሠራተኝነትም ቢሆን እያገለገሉ ለመኖር ቃል ገብተው እርዳታ እንዲደረግላቸው መማፀን ጀመሩ፡፡ ለጤና ተቋሙ ምስጋና ይግባውና ለግለሰቡ የመጀመሪያ የህክምና እርዳታ በማድረግ ለጊዜውም ቢሆን አካላቸውን ከስቃይ፣ ነፍሳቸውን ከሞት ታድጓቸዋል፡፡ በነገራችሁ ላይ፣ አንድ በመኪና አደጋ ጉዳት የደረሰበት ግለሰብ የመጀመሪያ የህክምና እርዳታ የሚያገኘው እንዴት ነው? ለቀጣይ ህክምና የሚሆን ገንዘብ ወይም አቅም ከሌለውስ ዕጣ ፈንታው ምንድነው? ዘጋቢው  የህብረተሰቡ አካል እንደመሆኑ ጥያቄዎቹም ከህብረተሰቡ ጥያቄዎች መሀል የተቆነጠሩ ናቸው፡፡

ከኚህ ግለሰብ የዕንባ ዘለላዎች ባሻገር የበርካቶች የዕንባ ጅረት የስንቶችን ጉንጭ እየተገማሸረ እንደሚፈስ ወንዝ የውሃ ሸለቆ ሰርቶበት ይሆን! ስንቶች የመጀመሪያ የህክምና እርዳታ ከተደረገላቸው በኋላ በአቅም ማነስ ክትትል ሳይደረግላቸው ከመንገድ ቀርተዋል፡፡ ደሞ'ንጂ የመጀመሪያ የህክምና እርዳታውንም ሳያገኙ ‹የወገን ያለህ!› እንዳሉ ወገን ሳይደርስላቸው እስከወዲያኛው የቀሩስ ስንቶች ይኖሩ ይሆን! በርግጥም እንዳሉ ጩኸታቸው ሞገዱን እያሰገረ የፌዴራል የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የምርመራ ቡድን ጆሮ መድረሱን ቡድኑ አንቀጽ አጣቅሶ፣ ምክንያት ሰጥቶ፣ አስረጅ አስቀምጦ ያሳየናል፡፡ የምርመራ ቡድኑ ከተሽከርካሪ አደጋ ጋር በተያያዘ የሰማውን ጩኸት ምክንያት ሊያጣራ፣ የበደሉንም ሥር ሊመረምር፣ ዕንባንም ሊያብስ፣ የመፍትሄ ሀሳብም ሊሰነዝር፣ ‹ማን፣ ምን፣ ለምን፣ እንዴት፣ መች፣ የት?› የሚሉትን የምርመራ ትጥቆች ታጥቆ ዘመተ - ወደ ምርመራ ግንባር፡፡

በመሆኑም፣ ከተሽከርካሪ አደጋ ጋር በተያያዘ ያሉ የአገልግሎት ክፍተቶችን በማስመልከት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዙሪያ በራስ ተነሳሽነት ምርመራዊ ጥናት (own-motion investigative research) በማድረግ ለችግሩ ዘለቄታ ያለው የመፍትሄ ሀሳብ ለመስጠት ረዥሙን ጉዞ ተያያዘው፡፡ ምርመራው ፈታኝና እልህ አስጨራሽ እንደሚሆን ከልምድ ቢያውቀውም የሚሠራው ለፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት አሰጣጥ፣ ለመልካም አስተዳደር መረጋገጥ፣ ለህዝብ ጥቅም፣ ለሀገር ዘላቂ ልማት፣ ባጠቃላይ ህግ አውጭው የሚያወጣቸው ህጎች በህግ አስፈጻሚው ተግባራዊ ሆነው የዜጎች ህገ መንግሥታዊ መብቶች እንዲረጋገጡ ነውና የሚገዳደረውን ኃይል ተቋቁሞ፣ ፈተናውን ለማለፍ ወሰነ፡፡ ለመሆኑ ከተጎጂው ግለሰብ ጋር የሚያያዘው ጉዳይ ምን ይሆን? ከህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ሥልጣንና ኃላፈነት ጋርስ እንዴት ይገናኛል? የዘጋቢው ተረክ ይቀጥላል . . .

የተሽከርካሪ አደጋ የህይወት ጥፋት፣ የንብረት ውድመትና የአካል ጉዳት ከሚያደርሱ አደጋዎች አንዱና ዘወትር የሚከሰት ነው፡፡ በየዕለቱ በሚከሰተው አደጋም እጅግ ከፍተኛ ሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እንደሚደርስ የተለያዩ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ የአሽከርካሪ ብቃት ማነስ፣ የሥነ ምግባር ጉድለት፣ የተሽከርካሪ ብቃት ችግር፣ የመንገድ (አስፋልት) ምቹ አለመሆን፣ ለእግረኛ ቅድሚያ አለመስጠትና የመሳሰሉት በምክንያትነት ከሚጠቀሱት መሃል ናቸው፡፡

በአደጋው የስንቱ ቤት እየፈረሰና የስንቱ ንብረት እየወደመ እንኳን አደጋው ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አይስተዋልም፡፡ ስንቶቹ በሰላም ወጥተው እንደወጡ ቀርተዋል፤ ወላጆቻቸው ወጥተው ሲመለሱ እጅ እጃቸውን ማየት የለመዱ ህፃናት ልጆች በር በሩን እየተመለከቱ የለመዱትን እጅ ናፍቀዋል፤ እናት ልጇን አጣጥባ፣ አልብሳ፣ ቁርሱን አብልታ፣ ምሳውን ቋጥራና ወደ ት/ቤት ሸኝታ ‹ሬሳሽን ታቀፊ› ተብላለች፡፡ ስንቶች ሙሉ አካላቸውን ይዘው ወጥተው ግማሽ አካላቸውን ይዘው ተመልሰዋል፡፡ ባጠቃላይ ስንቶች ህልማቸውን እውን ለማድረግ ወጥተው ቅዠት ሆኖባቸዋል- በተሽከርካሪ አደጋ!

ይነስም ይብዛ-ህይወትም ይቀጠፍ ንብረትም ይጥፋ አካልም ይጉደል- ብቻ በዚሁ ሳቢያ የብዙዎች ትዳር ከታለመው ሳይደርስ፣ የብዙዎች በኋቃ ጎድሎ ልጆች ለጎዳና፣ ለህፃናት ጉልበት ብዝበዛ፣ ለአስገድዶ መደፈርና ሌሎች ሰብዓዊና አስተዳደራዊ በደሎች ሲዳረጉ ሰምተናል፣ አይተናልም፡፡ ይህን በሀገርና በትውልድ ላይ የተቃጣ ተኩስ አልባ ጥቃት እንዳይደርስ ለመከላከል ከሚሰሩት ሥራዎች ጎን ለጎን የአደጋው ተጎጂዎች አስቸኳይ የህክምና አገልግሎት በመንግሥትና በግል የጤና ተቋማት እንዲያገኙና ለሚደርስባቸው የአካል ጉዳትና የሞት አደጋ ተገቢውን ካሣ በመስጠት በአደጋው ምክንያት ሊደርስባቸው የሚችለውን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ለመከላከል የተሽከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን ሽፋን አዋጅ ቁጥር 559/2000 እና የተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 779/2005 ወጥቶ በመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ ኃላፊነት ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ እየሆነ ይገኛል፡፡

አዋጁ በዋነኝነት በአፋጣኝ ህክምና እጦት በህይወት መትረፍ ሳይችሉ የሚቀሩትን ተጎጂዎች በማትረፍና ተገቢውን ካሣ በመስጠት ቀጣይ ህይወታቸውን የተስተካከለ ማድረግ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡ በአዋጁ መሠረት ማንኛውም የመንግሥትም ሆነ የግል የጤና ተቋም ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ለተጎጂዎች አፋጣኝ የመጀመሪያ የህክምና አገልግሎት መስጠት አለበት፡፡ ተቋሙ ያወጣው ወጪም በአዋጁ መሠረት የሚተካ ስለሆነ ተጎጂዎችን የቅድሚያ ክፍያ መጠየቅ አይጠበቅም፡፡ ይሁንና አዋጁ ቢኖርም ችግሩ አሁንም መታየቱ አንድ የአሠራር ችግር እንዳለ ያሳያል፡፡ ለህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የምርመራ ቡድን የምርመራዊ ጥናት መነሻ የሆነውም ይኸው የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ የፈጠረው ችግር ነው፡፡ ለመሆኑ የሦስተኛ ወገን የመድን ሽፋን እያለ ችግሩ እንዴት ሊከሰት ይችላል? የምርመራ ቡድኑ ምላሽ አለው፡፡ የዘጋቢው ተረክ ይቀጥላል . . .

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 55 ንዑስ አንቀጽ 15 መሠረት በአዋጅ ቁጥር 211/1992 የተቋቋመ ተቋም ነው፡፡ ዓላማውም በህግ የተደነገጉ የዜጎች መብቶችና ጥቅሞች በአስፈጻሚ አካላት መከበራቸውን በማረጋገጥ የህግ የበላይነትን መሠረት ያደረገ ጥራት ቅልጥፍናና ግልጽነት ያለው መልካም የመንግሥት አስተዳደር እንዲሰፍን ለማድረግ ነው፡፡ ተቋሙ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላትና ባለሥልጣናት በሚሰጡት ፍትሀዊነት የጎደለው አስተዳደራዊ እርምጃና ውሳኔ ሳቢያ በህዝብና በግለሰቦች ላይ አስተዳደራዊ በደል ማድረስ አለማድረሳቸውን በማጣራት እንዲታረሙ የምርመራ ሥራ ያከናውናል፡፡

በመሆኑም ተቋሙ በዜጎች ላይ የሚደርሱ አስተዳደራዊ በደሎችን አስመልክቶ የሚቀርቡ አቤቱታዎችን/ጥቆማዎችን ተቀብሎ ምርመራ ያደርጋል፡፡ በደል ስለመፈጸሙ ጥርጣሬ በሚኖረው ጊዜም በራስ ተነሳሽነት ምርመራዊ ጥናት ማድረግ እንደሚችል በተቋሙ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 211/92 አንቀጽ 24 ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ በዚሁ መሠረት ላለፉት ዓመታት በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተቶች ላይ ምርመራዊ ጥናቶች በማካሄድ የጥናቶቹን ግኝቶች ከነመፍትሄዎቻቸው ለተቋማቱ በማቅረብና በማሳወቅ የአገልግሎት አሰጣጡ እንዲሻሻልና መልካም የመንግሥት አስተዳደር እንዲሰፍን የበኩሉን ሚና ሲጫወት ቆይቷል፡፡ የአሁኑ ምርመራም የዚሁ አካል ነው፡፡

የምርመራ ቡድኑ፣ አዋጁ ቢኖርም ችግሩ አሁንም መታየቱ አንድ የአሠራር ችግር እንዳለ በመጠርጠሩ በደረሰው ጥቆማ መሠረት የመጀመሪያ የምርመራ መረቡን በጤና ተቋማት ላይ መጣሉ አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘው ኢላማውን በተጠረጠሩ የፌዴራልና የክልል የመንግሥትና የግል ሆስፒታሎችና የጤና ተቋማት ላይ አደረገ፡፡ በዚሁ መሠረት በአዲስ አበባ በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታልና በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል፣ በአማራ የባህር ዳር ፈለገ ህይወት ሆስፒታልና ኪዳነ ምህረት የግል ከፍተኛ ክሊኒክ፣ በደቡብ የወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ አተና የመንግሥት ሆስፒታልና ክርስቲያን የግል ሆስፒታል፣ በሀዋሳ የአደሪ የመንግሥት ሆስፒታል እንዲሁም በኦሮሚያ የአዳማ ሆስፒታልን ጓዳ ጎድጓዳ መበርበሩን ተያያዘው፡፡ በምርመራው ሂደት የጥርጣሬው ፍንጮች መታየት ጀመሩ፡፡ ከየጤና ተቋማቱ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በተሽከርካሪ አደጋ የደረሰባቸው ተጎጂዎች ወደ ተቋማቸው ሲመጡ በተሽከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን ዋስትና አዋጅ መሠረት አስቸኳይ የህክምና አገልግሎት እየሰጡ አለመሆኑ፣ በአዋጁ መሠረት ለተጎጂዎች አገልግሎት ከሰጡ በኋላም ቢሆን ያወጡትን ወጪ ተመላሽ ለመጠየቅ የሚያስችል ግልጽ የሆነ የአሰራር ሥርዓት አለመኖሩ፣ በተሽከርካሪ አደጋ የደረሰባቸው ተጎጂዎችም በአዋጁ መሠረት ለደረሰባቸው የአካልና የሞት ጉዳት ተገቢውን የካሳ ክፍያ እያገኙ አለመሆናቸውና ሌሎች ነጥቦች በምርመራው ወረንጦ ተነቅሰው ወጡ፡፡ ግን ለምን?

ተጎጂዎች አስቸኳይ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙና ለደረሰባቸው የአካልና የሞት ጉዳትም ተገቢው ካሳ እንዲከፈላቸው፣ የህክምና ተቋማቱም አገልግሎቱን ከሰጡ በኋላ ያወጡት ወጪ እንደሚተካላቸው በአዋጁ ላይ ተቀምጧል፡፡ የጤና ተቋማቱ ወጪ የሚሸፈነውም አደጋውን ያደረሰው ተሽከርካሪ የሦስተኛ ወገን መድን ሽፋን የተገባለት ከሆነና የታወቀ (የተያዘ) ከሆነ ኢንሹራንስ ከገባበት ኩባንያ (ድርጅት) መጠየቅ እንደሚችሉ፣ የሦስተኛ ወገን የመድን ሽፋን ያልገባ ከሆነ ወይም ገጭቶ ያመለጠ ከሆነ ደግሞ የመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲውን በመጠየቅ ገንዘባቸው ተመላሽ እንደሚሆን አዋጁ ላይ ሰፍሯል፡፡ ቢሆንም የህክምና ተቋማቱ በአራት ዋና ዋና ምክንያቶች በአዋጅ የተጣለባቸውን ግዴታ እየተወጡ አለመሆኑን የምርመራው ወንፊት በሚገባ እያንጓለለ ለየው፡፡

የመጀመሪያው ምክንያት፣ ከፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚ/ር፣ ከክልል የጤና ቢሮ ኃላፊዎች፣ ከመንግሥትና የግል የህክምና ተቋማት ባለሙያዎችና ከተገልጋዮች ጋር በተደረገ ቃለ መጠይቅና የመስክ ምልከታ የህክምና ተቋማቱ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ስለ አዋጁ በቂ ግንዛቤ እንደሌላቸው ታወቀ፡፡ በመሆኑም የጤና ባለሙያዎቹ አገልግሎቱን ያለምንም ቅድመ ሁኔታና ወጪ ለተጎጂዎች የመስጠት ግዴታ እንዳለባቸው ባለመረዳት አገልግሎቱ በአዋጁ መሠረት እየተሰጠ አለመሆኑ ሊረጋገጥ ችሏል፡፡ ሁለተኛ ምክንያት፣ ማንኛውም የተሽከርካሪ አደጋ የደረሰበት ተጎጂ በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 779/2005 አንቀጽ 27 መሠረት አስቸኳይ የህክምና አገልግሎት ማግኘት እንዳለበት የተደነገገ ቢሆንም፣ በቅድምያ ገንዘብ እንዲያሲዝ፣ ውል እንዲገባና ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎችን እንዲያሟላ ይጠየቃል፡፡ ይሁንና አገልግሎቱን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በነፃ የማግኘት መብት እንዳለው በማስረዳት በመብቱ ከመጠቀም ይልቅ የተጠየቀውን ለማድረግ ደፋ ቀና ሲል ይታያል፡፡ ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱም፣ የመድን ፈንድ ኤጀንሲው የተሽከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን ሽፋን ዋስትና አዋጁን መሠረት በማድረግ የተሽከርካሪ አደጋ ለሚደርስባቸው ተጎጂዎች አስቸኳይ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ያስችል ዘንድ የማስፈጸሚያ መመሪያ ቢያወጣም መመሪያው ወደ ተግባር እንዲገባ አገልግሎቱን ከሚሰጡ የህክምና ተቋማትና ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር ሰፊ የቅንጅት ሥራዎች ባለመሰራታቸው ስለ አሰራሩ የግንዛቤ ችግር ሊፈጠር መቻሉ ነው፡፡

ሦስተኛው፣ የመድን ፈንድ ኤጀንሲ፣ የህክምና ተቋማት አገልግሎቱን በህጉ መሠረት ስለመፈጸማቸው፣ ተጎጂዎችም መብታቸውን መጠቀማቸውን አስመልክቶ አዋጁን እንዲያስፈጽምና እንዲከታተል ኃላፊነት የተጣለበት ቢሆንም ከሀገሪቱ የቆዳ ስፋት፣ በቂ የሆነ የበጀት እጥረትና ኤጀንሲው ካለው አደረጃጀትና የሰው ኃይል ቁጥር ማነስ ጋር በተያያዘ በሚገባ አለመወጣቱ ታውቋል፡፡ በዚህም ሳቢያ ተጎጂዎች በአዋጅ የተሰጣቸውን ነፃ የአስቸኳይ የህክምና አገልግሎት እንዳያገኙ ከማድረጉም ባሻገር በአረቦን መልክ ከተሽከርካሪ ባለንብረቶች የሚሰበሰበው ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ ከመዋል ይልቅ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን ካዝና ማደለቢያ እየሆነ እንደሚገኝ ጥናቱ አረጋግጧል፡፡ የመጨረሻው ምክንያት፣ በሀገሪቱ የሚገኙ የመንግሥት የህክምና ተቋማት ዓመታዊ በጀት የሚሸፈነው በአብዛኛው ከተገልጋይ ከሚሰበሰብ የአገልግሎት ክፍያ ነው፡፡ የተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂን ለማዳን የሚሰጠው የህክምና አገልግሎት ደግሞ በባህሪው ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ነው፡፡ የህክምና ተቋማቱ ለተጎጂዎች በነፃ አስቸኳይ የህክምና አገልግሎት የመስጠት ግዴታ እንዳለባቸው ቢያውቁ እንኳን ከላይ በተገለጸው የበጀት እጥረት ምክንያት አገልግሎቱን እየሰጡ አለመሆኑን ከምርመራው ውጤት  ለማረጋገጥ ችሏል፡፡ በተጨማሪም የህክምና ተቋማቱ ያወጡት ወጪ የሚሸፈንበት አሠራር ግልጽ አለመሆኑም ለክፍተቱ መስፋት እንደ ምክንያት ይጠቀሳል፡፡

ሌላው ጉዳይ ለአካልና ለሞት ጉዳት የሚፈከፈለው የካሳ ክፍያ ነው፡፡ የተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች አስቸኳይ የህክምና አገልግሎት ከማግኘት በተጨማሪ እስከ 40,000.00 (አርባ ሽህ ብር) የሚደርስ የጉዳት ካሳ የማግኘት መብት እንዳላቸው በአዋጅ 779/2005 አንቀጽ 16 መሠረት በግልጽ ተደንግጓል፡፡ ይሁንና ተጎጂዎችና ቤተሰቦቻቸው በአዋጁ ላይ በቂ የሆነ ግንዛቤ ስለሌላቸው በግል ከአሽከርካሪውና ከተሽከርካሪው ባለንብረት ጋር በመደራደር ካሳ ለማግኘት ጥረት እንደሚያደርጉ ተደርሶበታል፡፡ ግንዛቤው ያላቸውም ቢሆኑ በአዋጁ ላይ የተጠቀሰው የካሳ መጠን በጣም አነስተኛ ነው በሚል ወደ መድን ፈንድ ኤጀንሲና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከማቅረብ ይልቅ የካሳ ጥያቄያቸውን በግል በመደራደር ለመጨረስ ጥረት እንደሚያደርጉ የምርመራ ቡድኑ አረጋግጧል፡፡ በአጠቃላይ የመድን ፈንድ ኤጀንሲ ተጎጂዎች ለደረሰባቸው አደጋ ተገቢውን ካሳ እንዲያገኙ በተጎጂዎችም ሆነ በኢንሹራንስ ኩባንያዎች ወገን ተገቢ የሆነ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየተሰራ አለመሆኑና ከተሽከርካሪ ባለንብረቶች የሚሰበሰበው ገንዘብም የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን ኪስ ከመሙላት ባለፈ የተጎጂዎችን መብት እያስከበረ አለመሆኑን የምርመራ ቡድኑ አረጋግጫለሁ ሲል ጥናቱን ቋጭቷል፡፡ ተቋሙ የመድን ፈንድ ኤጀንሲን ከሌሎች ግብረ አበሮቹ ጋር በማገናኘት የካቲት 7 ቀን 2006 ዓ.ም. በግሎባል ሆቴል አዳራሽ ውስጥ የጥናቱን ግኝት አስደምጧል፡፡ የዘጋቢው ተረክ ቱባው እንዲህ ይጠቀለላል . . .

የመድን ፈንድ ኤጀንሲ፣ የጤና ተቋማት፣ የፖሊስ ኮሚሽን፣ መንገድ ትራንስፖርትና ኢንሹራንስ ኩባንያ እንደዚሁም ጉዳዩ ያገባናል የሚሉ ባለድርሻ አካላት ሁሉ በችግሩ ዙሪያ ለመምከርና ለመዘከር በአዳራሹ ውስጥ በአንድነት ታደሙ፡፡ በርግጥም የአደጋው ስፋትና ጥልቀት በባለድርሻ አካላቱ ሥልጣንና ኃላፊነት ልክ የተሰፋ ይመስላል፡፡ የመንገድ አስተማማኝነት፣ የፖሊስ ፈጥኖ ደራሽነት፣ የጤና ተቋማት ለወገን ተቆርቋሪነት፣ የኢንሹራንሶች እጀ ረዥምነት፣ የመድን ፈንድ ፊታውራሪነት የችግሩን ስፋት ሊያጠብ ጥልቀቱንም ሊሞላ ይችላል- ህብረቱ ካለ፣ ጥምረቱ ካለ፡፡

ጥናቱ በቀረበበት ወቅት ችግሩ ወዴት ይወድቃል የሚለውን ሁሉም ለማጤን ሞክረዋል፡፡ ችግሮች መኖራቸውን ከመተማመን ባሻገር የየድርሻቸውን ቆንጥረው ወስደዋል፡፡ የመድን ፈንድ ኤጀንሲ የበጀትና የሰው ኃይል እጥረት ስላለበት አድማሱን በሚገባ አለማስፋቱ፣ የጤና ተቋማት ላይ ሰፊ የግንዛቤ ሥራ አለመሰራቱ፣ ፖሊስ ከህይወት ደህንነት ይልቅ ለአደጋው መንስኤ ቅድሚያ ወደ መስጠት ማዘንበሉ፣ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከህይወት ደህንነት ይልቅ ለካዝና ደህንነት ቅድሚያ መስጠታቸው፣ የአስፋልቶች (የመንገዶች) ደህንነት ችግርና የመሳሰሉት በሚገባ ታሽተው፣ ተበጥረው፣ ተፈጭተውና ተቦክተው ተጋገሩ፡፡ ከእንግዲህ ስንፈተ ጥምረትና ውህደት ሳያሸንፋቸው፣ እጅ ለእጅ ተያይዘው፣ ጀርባ ለጀርባ ተደጋግፈው፣ ደንደሳቸውን አፈርጥመው የወገንን ህይወትና ንብረት ለመታደግ በድጋሚ ቃል ገብተዋል፡፡ አደጋው የሁሉንም ደጃፍ የሚያንኳኳ እንደመሆኑም ህዝቡም ሆነ ሌሎች ተቋማት በሙሉ የድርሻቸውን እንዲወጡም አደራ ሰጥተዋል፡፡ የተቋሙ የምርመራ ባታሊዮንም ግዳጁን እንደተወጣ ፊቱን ወደ ሌላ የምርመራ ግንባር አዞረ!

ማን ይናገር- አንባቢው፣

ማን ይስማ- ጆሮ ያለው!

 

የምርመራ ጥናት፡- የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የአስተዳደር በደል ማረም ዳይሬክቶሬት

መጨረሻ የተሻሻለው በ አርብ, 31 October 2014 08:43