ሀተታ
የአካል ጉዳተኞችና ማኅበራዊ አገልግሎቶች ከህገ መንግሥታዊ መብትና ጥቅም አንፃር
አርብ, 24 July 2015 09:27

አካል ጉዳተኞች ባጋጠማቸው ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ ችግር ምክንያት ለተለያዩ የሥነ ልቦናዊ፣ አካላዊ፣ መህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሲጋለጡ ይስተዋላል፡፡

አካል ጉዳተኞችን በተገቢው መንገድ በመንግሥት አገልግሎቶች ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ያደረጓቸው ውስብስብ ምክንያቶች አሉ፡፡ ህንፃዎችና መንገዶች ሲገነቡ አካል ጉዳተኞች እንደ አካል ጉዳታቸው ዓይነት ሊጠቀሙባቸው የሚችሉበትን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት የሚከናወኑ ባለመሆኑ አካል ጉዳተኞች የመሠረተ ልማቶች ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ተደርገዋል፡፡

በርካታ ህዝብ የሚገለገልባቸው ትላልቅ ህንፃዎች ማለትም የትምህርት ተቋማት፣ ሆስፒታሎች፣ የገበያ አዳራሾች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችና የመኖሪያ አፓርትመንቶች ሲሰሩ ለአካል ጉዳተኞች በአብዛኛው የሚያመቹ ሆነው አይገኙም፡፡

በተጨማሪም፣ የመፀዳጃ ክፍሎቻቸው ለአካል ጉዳተኞች በተለይም ለዊልቸር ተጠቃሚዎች ምቹ ሆነው ባለመሠራታቸው አገልግሎቱን ሰንካላ ያደርገዋል፡፡ መንገዶች ሲሰሩ ለዊልቸር ተጠቃሚዎችና ማየት ለተሳናቸው ምቹና በተወሰነ ርቀት ከደረጃ ነፃ (ልሙጥ) ሆነው ስለማይሰሩ ዊልቸር ተጠቃሚ አካል ጉዳተኞች ለመውረድና ለመውጣት ሲቸገሩና የመንገደኞችን ትብብር ሲጠይቁ ይታያል፡፡ከዚህ ጋር በተያያዘም በእግረኛ መንገድ ላይ ያልተደፈኑ በርካታ ጉድጓዶች ስለሚኖሩ ማየት የተሳናቸው ለአደጋ ሲጋለጡ ይስተዋላል፡፡

እነዚህን ችግሮች ሁሉ ከግምት ውስጥ በማስገባትና ሁሉም ዜጎች በሀገሪቱ እኩል ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የኢፌዲሪ ህገ መንግሥት አንቀጽ 25 ሁሉም ዜጎች በህግ ፊት እኩል መሆናቸውንና በመካከላቸው ማንኛውም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግ በህግ እኩል ጥበቃ እንደሚደረግላቸው ይደነግጋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በአንቀጽ 41/3 የኢትዮጵያ ዜጎች ሁሉ በመንግሥት ገንዘብ በሚካሄዱ ማህበራዊ አገልግሎቶች በእኩልነት የመጠቀም መብት እንዳላቸው ይደነግጋል፡፡ በዚሁ አንቀጽ በንዑስ አንቀጽ 41/5 ላይ መንግሥት የአካልና የአእምሮ ጉዳተኞችን ለማቋቋምና ለመርዳት የሀገሪቱ አቅም በፈቀደው ደረጃ እንክብካቤ እንደሚደረግ ይደነግጋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የማህበራዊ ደህንነት ልማት ፖሊሲ የአካል ጉዳተኞችን ተደራሽት በተመለከተ በሥራ አካባቢ፣ በመኖሪያ ሥፍራዎችና እንደ አስፈላጊነቱ በሌሎች ቦታዎች የአካል ጉዳተኞችን እንቅስቃሴ የሚገድቡና የሚገቱ መሰናክሎች ደረጃ በደረጃ እንዲወገዱ ጥረት ይደረጋል ይላል፡፡ እነዚህ ሁሉ የህግ ማዕቀፎች በመኖራቸው የአካል ጉዳተኞችን ተደራሽነት ችግር ለመቅረፍ የሚደረጉ ጥረቶች ቢኖሩም በሚፈለገው ደረጃ ላይ ደርሰዋል ለማለት አይቻልም፡፡

ሀገራችን የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነትና ተደራሽነት ለማረጋገጥ የሚያስችል የአካል ጉዳተኞች የሥራ ስምሪት አዋጅ ያወጣች ሲሆን በአዋጁም ተመጣጣኝ የሆነ ምቹ የሥራ ሁኔታ ካለመፈጠሩ የተነሳ አካል ጉዳተኞች በእኩል የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ባለመሆናቸው የሚፈጠር የሥራ ዕድል መጣበብ መድልዎ እንደመፈጸም ይቆጠራል ብሎ ይደነግጋል፡፡ በመሆኑም የአካል ጉዳተኞችን የአገልግሎት ተደራሽነት ለማረጋገጥ በተለያዩ ዘርፎች የሚቀየሱ ፖሊሲዎችና ህጎች የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት አካተው ሊወጡ ይገባል፡፡ ለፖሊሲና ለህግ አውጪዎች፣ ለዲዛይነሮች፣ ለህንፃ ተቋራጮች፣ ለምህንድስና ባለሙያዎች፣ ለባለሀብቶችና ባለድርሻ አካላት ሰፊ የግንዛቤ ማዳበሪያ ተግባራትን በየደረጃው ማከናወን፤ የባለ ድርሻ አካላትን ቅንጅት ማጠናከርና የወጡ ህጎች በአግባቡ እንዲተገበሩ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ የአካል ጉዳተኞችን ተደራሽነት ችግር ለማቃለል አዎንታዊ እርምጃዎች ናቸው፡፡

የአካል ጉዳተኞች እንደማንኛውም ዜጋ በኢኮኖሚያዊ፣ በማህበራዊና በፖለቲካዊ መስኮች የመሳተፍና የበኩላቸውን አስተዋፅኦ የማበርከት ህገ መንግሥታዊ መብት ያላቸው መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የአካል ጉዳተኞችን እኩል ዕድልና ሙሉ ተሳትፎ እውን ለማድረግ ከሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎ አንዱ ተደራሽነትን መፍጠር ነው፡፡ የአካል ጉዳተኞችን ህገ መንግሥታዊ መብትና ጥቅም ለማስከበር የወጡ ህጎችና ፖሊሲዎች በአስፈጸሚው አካላት በኩል በትክክል መተግበራቸውን ማረጋገጥ፣ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የሥራ እንቅስቃሴ አንድ አካል ነው፡፡ ተቋሙም ዜጎች አስተዳደራዊ በደል እንዳይደርስባቸውና በደል ደርሶባቸውም ከተገኘ እንዲታረምላቸው ለማስቻል በሚያደርገው ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎች ውስጥ አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ ተደራሽነቻውንና ተጠቃሚነታቸውን እውን ለማድረግ በመስኩ የበለጠ ቅርበት ያላቸውን የመሠረተ ልማት ግንባታ ተሳታፊ የሆኑ ዲዛይነሮች፣ ህንፃ ተቋራጮች፣ ለምህንድስና ባለሙያዎች፣ አርክቴክቶችና ባለሀብቶች እንዲሁም ለሚመለከታቸው የመንግሥት አስፈጻሚና ህግ አውጪዎች በአካል ጉዳተኞች ተደራሽነትና የመብት ተጠቃሚነት ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች በማዘጋጀት እንዲሁም አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ የወጡ ህጎች አፈጻጸም ላይ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ላይ የሚገኝ ሲሆን በመስኩም አበረታች ውጤቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመዘገቡ መሆናቸውን ለመረዳት ይቻላል፡፡

የአካል ጉዳተኞችን ተደራሽነት ለማረጋገጥ ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግሥታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም መላው ህብረተሰብ የጋራ ግንዛቤ በመውሰድ የአካል ጉዳተኞችን ዘርፈ ብዙ ችግሮች በመቅረፍ ለሀገር ኢኮኖሚ የበኩላቸውን ሊያበረክቱና እነሱም ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉበትን ሁኔታዎች ማጎልበት ይገባል፡፡ የአካል ጉዳተኞች ህገ መንግሥታዊ መብቶች ተረጋግጠው በማናቸውም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚና ተሳታፊ እንዲሆኑ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም እንደ እስካሁኑ ሁሉ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ይሰራል፡፡

መጨረሻ የተሻሻለው በ አርብ, 24 July 2015 09:34
 
መልካም አስተዳደር ለዘላቂ ልማት
አርብ, 24 July 2015 07:05

የመልካም አስተዳደር ጽንሰ ሀሳብ መንግሥታት ለሚኖሯቸው ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አጀንዳዎች ከሚያስቀምጧቸው መመዘኛዎች አንዱ ሲሆን፣ መንግሥታቱ እንደሚከተሏቸው ሥርዓቶች የተለያየ ትርጓሜ ይሰጠዋል፡፡ ነገር ግን እንዳጠቃላይ የመልካም አስተዳደር መርሆች የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት የህግ የበላይነትን ሊያረጋግጥ በሚችል መልኩ ኃላፊነታቸውን የመወጣትና የሀገርን አንጡራ ሀብት የመቆጣጠር ጉዳይ ላይ ማትኮር እንደሚገባቸው በተለይ የዲሞክራሲን ሥርዓት የሚከተሉ ሀገሮች ይስማሙበታል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ጽ/ቤት የሰብዓዊ መብቶች የበላይ ኮሚሽነር (UN Human Rights Office of the High Commissioner for Human Rights) ‹‹…መልካም አስተዳደር ልማታዊ ግቦችን ከሚያሳኩ ፖለቲካዊና ተቋማዊ ፋይዳዎች ጋር በቀጥታ የሚቆራኝ ነው…›› በሚል ሀሳቡን ያጠናክረዋል፡፡ ኮሚሽኑ በ2000/64 ድንጋጌው ልማት/ዕድገት መንግሥታት እንደ መብት ሊያዩት የሚገባ ጉዳይ ነው የሚል አቋም ሲይዝ፣ ለስኬታማነቱም በተጠያቂነት፣ በአሳታፊነትና በህግ የበላይነት መንፈስ መሥራት እንደሚገባ ያስገነዝባል፡፡ በዚህም መልካም አስተዳደርን ቀጣይነት ካለው ልማታዊ እንቅስቃሴ ጋር ያያይዘዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (United Nations Development Program/UNDP) በበኩሉ፣ መልካም አስተዳደር በፍትሀዊነትና ውጤታማነት መርህ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በማህበረሰቡ ሁሉ አቀፍ መግባባትና ስምምነት ሲረጋገጡ ልማታዊ ትርጉም እንደሚኖራቸው ያስቀምጣል፡፡ በተለይ በሀገራዊ ሀብት አደላደልና አጠቃቀም ላይ የድሀውና የታችኛው ህብረተሰብ በውሳኔ አሰጣጡ ውስጥ የሚኖረው ተሳትፎ በልማቱ ቀጣይነት የሚኖረው አስተዋፅኦ የጎላ እንደሆነም ያሰምርበታል፡፡

የኢፌዲሪ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በአዋጅ የተቋቋመበት ዋነኛ ዓላማም በህግ የተደነገጉ የዜጎች መብቶች እና ጥቅሞች በአስፈጻሚው አካላት መከበራቸውን በማረጋገጥ፣ የህግ የበላይነትን መሠረት ያደረገ ጥራት፣ ቅልጥፍናና ግልጽነት ያለው መልካም የመንግሥት አስተዳደር እንዲሰፍን ማድረግ መሆኑም ከዚሁ የሚመነጭ ነው፡፡ በመሆኑም ተቋሙ አስፈጻሚ አካላት የሚያወጧቸው አስተዳደራዊ መመሪያዎች፣ የሚሰጧቸው ውሳኔዎችና አሠራሮቻቸው የዜጎችን ህገ መንግሥታዊ መብቶችና ህጎችን የማይቃረኑ መሆናቸውን ይቆጣጠራል፣

ትክክለኛ የሀብት ቁጥጥርና አጠቃቀም፣ ዜጎችን በእኩልነትና ፍትሀዊ በሆነ መልኩ ተጠቃሚ የሚያደርግ ዘላቂ ልማት የሚረጋገጥበት ነው፡፡ በርግጥም ለልማት ዋስትና የሚሰጥ ከመልካም አስተዳደር የሚነፃፀር ምንም ነገር ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ምክንያቱም ዘላቂ ልማትን የዜጎችን ፍላጎት ሊያሟላ በሚችልበት አቅም ለማሳደግ የመልካም አስተዳደር መኖር አጠያያቂ አይሆንምና ነው፤ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በራሱ ዘላቂ ልማትን አያመላክትምና፡፡ የልማት ዘላቂነት የሚለካው ዜጎች ከልማቱ ፍሬ እኩል ተጠቃሚ በሚሆኑበት ደረጃ ብቻ ስለሚሆን ማለት ነው፡፡ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዓላማ የዜጎችን መብቶችና ጥቅሞች ማስጠበቅ ነው ሲባልም ግቡ የዜጎችን ከብሄራዊ ሀብት እኩል ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው፡፡

የልማታዊ ኢኮኖሚ መሠረታዊ ዓላማ ዜጎች በእኩልነትና በፍትሀዊነት ከብሄራዊ ሀብት የሚጠቀሙበት ራስን የመቻልና ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ ነው፤ በዚህም ፍትሃዊ አሠራርን በዘላቂነት መዘርጋት ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ልማታዊ ኢኮኖሚ በሴቶችና በወንዶች እንዲሁም በአጠቃላይ ማህበረሰቡ መሃል ልዩነት የሌለበት የሀብት አጠቃቀም ዕድልን ይፈጥራል ተብሎም ይታመናል፡፡

ከዚህ ትንታኔ በመነሳት የልማታዊ ኢኮኖሚ ማጠንጠኛ የሀብት ክምችትን ማጋበስ ሳይሆን፣ ዜጎች በሀገራዊ ልማታዊ አጀንዳ ውስጥ ሊኖራቸው የሚገባውን ድርሻ ማሳደግ ነው በሚል ማጠቃለል ይቻላል፡፡ በመሆኑም ዜጎች በሀገራዊ ልማት ውስጥ እንደ ፈጻሚም እንደ ተጠቃሚም በስፋት ለመሳተፍ ፈቃደኛ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዚህም የመልካም አስተዳደር መስፈን የሚጫወተው ሚና እጅግ የጎላ ይሆናል፡፡ ስለዚህ የአንድ ሀገርን ልማታዊ ግሥጋሤ በዘላቂነት ለማስቀጠል የመልካም አስተዳደር መርሆችን ተግባራዊ ማድረግ አጠያያቂ አይሆንም፡፡

 
የመልካም አስተዳደር ሦስቱ ተዋንያን
አርብ, 24 July 2015 07:01

የአንድን ማህበረሰብ የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል መልካም አስተዳደርን ማረጋገጥ ዲሞክራሲያዊ መርህ ከሚባሉት መካከል አንዱና ወሳኙ ነው፡፡ እንደ ዲሞክራሲያዊ ፍልስፍናና አስተምህሮ ልማትና ዕድገትን ከመልካም አስተዳደር ነጥሎ ማየት ዘበት ነው፡፡ ይህም ሲባል፣ የትኛውንም ያህል ዕድገት ቢመዘገብ፣ የትኛውንም ያህል ልማት ቢመጣ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ከሌለ ትርጉም አልባ ይሆናል ለማለት ነው፡፡ መልካም አስተዳደር ደግሞ ለፍትሀዊ የሀብት ክፍፍልና ለዜጎች እኩል ተጠቃሚነት ቁልፍ መሣሪያ ነው፡፡ ታዲያ፣ ለስኬታማነቱ የሦስት ነገሮች ጥምረት የግድ ያስፈልጋል፡- የህግ፣ የህግ ተፈጻሚነትና የህዝብ ተሳታፊነት፡፡ ከነዚህ ነጥቦች ጀርባ ደግሞ መንግሥት፣ አስፈጻሚው አካልና ህዝቡ ሲኖሩ የአንዳቸው ተሳትፎ መጉደል ስኬቱን ሊያደናቅፍ ይችላል፡፡

ወደ ነጥቡ ስንመጣ፣ በቅድሚያ የድንጋጌዎች መኖርና ድንጋጌዎቹን የማስፈጸም አቅም ያለው ጠንካራ መንግሥት ያስፈልጋል፡፡  ህጎች ሲኖሩ፣ መመሪያዎችና ደንቦች ሲቀረጹ ለመልካም አስተዳደር መስፈንና ለዜጎች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መረጋገጥና ተጠቃሚነት የመጀመሪያው መደላድል ይፈጠራል፡፡ ይህ ጉዳይ በህገ መንግሥታችን ስለ መሠረታዊ የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች በሚያትተው አርቲክል ላይ በግልጽ ሰርፎ ይገኛል፡፡ ይሁንና የህጎቹ መኖር በራሱ ምሉዕ አይሆንምና ለተፈጻሚነታቸው የመንግሥትን ጥብቅ ክትትልና ድጋፍ ይጠይቃል፡፡

በመቀጠልም፣ የመንግሥት አካላት በወጡ መመሪያዎች፣ ፖሊሲዎችና ደንቦች መሠረት በግልጽነትና ተጠያቂነት መርህ የተሰጣቸው ኃላፊነት መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ዜጎችን በማገልገል ሂደት ውስጥ የግልጽነት መኖር በህዝብ ዓይን ታማኝነትን ከማጎናጸፉም በላይ በአስፈጻሚው አካል ዘንድ ደግሞ የተጠያቂነትን ስሜት ያሳድጋል፡፡ ምክንያቱም፣ የጉዳዩ ዋነኛ ተጠቃሚም ሆነ ተጎጂ ህዝቡ እስከሆነ ድረስ የተገኙ ውጤቶች ላይም ሆነ የሚፈጠሩ ችግሮች ላይ ግንዛቤ ያስፈልገዋል፡፡

በሦስተኛ ደረጃ፣ በማንኛውም የመንግሥታዊ አካል እንቅስቃሴ ውስጥ የህዝብ ተሳትፎ መኖር መልካም አስተዳደርን ለማስፈን በሚደረገው ትግል ውስጥ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል፡፡ በአሳታፊነት መርህ መሠረት ዜጎች መንግሥታዊ አካላቱ ስለሚተገብሩት ብሎም ለህብረተሰቡ ስለሚሰጡ አገልግሎቶች የማወቅ መብት ሲኖራቸው መንግሥታዊ አካላቱ ደግሞ ይህንኑ የማሳወቅ ግዴታ አለባቸው፡፡ የዜጎች ተሳትፎ የመብት ጉዳይ ብቻም አይደለም፤ አስፈጻሚው አካል የሚተገብራቸው ተግባራት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በዜጎች ላይ ከሚያሳድሩት አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ አንፃር ዜጎች ይህንኑ የመጠየቅና የመከታተል ግዴታቸውም ነው፡፡ በመሆኑም ሀሳባቸውን በግልጽና በነፃነት የሚሰነዝሩበት ምቹ ሁኔታ ሊፈጠር የግድ ነው፡፡ ይህ ሲሆን፣ ሁሌም የተሻለ አገልግሎት ለመፈለግ የሚተጋ ህብረተሰብ መፍጠር ያስችላል፡፡

ባጭሩ፣ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መዳበር፣ ለዘላቂ ሰላም መስፈን፣ ቀጣይነት ላለው ልማት መሳካት የለመልካም አስተዳደር መረጋገጥ አጠያያቂ ያለመሆኑን ያህል፣ ለመልካም አስተዳደር መኖር የሦስቱ የመልካም አስተዳደር ተዋንያን መኖርና በጣምራ መሥራት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ የአንዳቸው መጉደል ሂደቱን ወደኋላ ከመጎተት ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አስፈጻሚ አካላት ሥራቸውን በህግ አግባብ በማከናወን ለዜጎች ተገቢው አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ከመቆጣጠር ባሻገር ከላይ ለተጠቀሱት አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችንም ያዘጋጃል፡፡ ይህ የሚሆነው ሁሉም የየድርሻውን በመረዳት መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥ በሚደረገው ትግል ውስጥ በቅንጅት መሥራት እንዳለበት ለማስገንዘብ ነው፡፡

 
በፆታዊ መድልዖ ተጎጂው ህብረተሰቡ ነው!
አርብ, 24 July 2015 06:50

ሰለጠነ በሚባለው በዚህ ዘመን ሳይቀር፣ ሰለጠኑ በሚባሉት ሀገሮች ጭምር፣ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን (ማርች 8) በመላው ዓለም መከበር ከጀመረ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ቢያስቆጥርም ፆታን ዒላማ ያደረገ መድልኦ መልኩን እየቀያየረ መከሰቱን አልተወም፡፡ ወሲባዊ ጥቃት፣ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጥቃት፣ የሴት ልጅ ግርዛት፣ ያለዕድሜ ጋብቻ፣ ያላቻ ጋብቻ፣ ዛቻ፣ ትንኮሳና ሌሎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህ ድርጊት ከቤት ይጀምርና፣ ወደ ጎረቤት ይዛመትና በትምህርት ቤቶች፣ በሥራ ቦታዎች፣ ወዘተ፣ ወዘተ፣ እያለ ጠባሳውን ሴት እህቶቻችን ላይ ጥሎ ያልፋል፤ ይህ ድርጊት እንደ ባለሁለት ምላስ ሰይፍ ባንድ ጎኑ ሴቷን ሲገዘግዝ፣ በሌላ ጎኑ የሰው ዘርን በሞላ እየጎዳ ከትውልድ ትውልድ ይዛመታል፡፡ ይህ ድርጊት ትውልድ ሊመክተው፣ ክስተቶች ሊለውጡት፣ ባህል ሊቀይረው፣ አመለካከት ሊያስተካክለው፣ ጊዜና ሥፍራ ሊቆጣጠረው ሲችል ከትገሉ ዕድሜ አንጻር አዝጋሚ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

በዚህም ሳቢያ ሴቷ መሠረታዊ ሰብዓዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ግላዊ መብቶቿ፡- አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ስብዕናዋ፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግሥጋሤዋ፤ የሴትነትና የሰብዓዊ ክብሯ በሚፈለገው ደረጃ ተጠብቆ እምቅ እውቀቷንና ኃይሏን አሟጦ ለመጠቀም አልተቻለም፡፡ ድርጊቱ በሴቷ ላይ የተነጣጠረ ይሁን እንጂ በመላው የሰው ልጅ ዘር ላይ የተሰበቀ ጦር ነው፤ ምክንያቱም ዓለማችን በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች የተረጋጋች እንድትሆንና ለነዋሪዎቿ ምቹ ሥፍራ እንድትሆን ብቸኛው መንገድ ህዝቦች ሁሉ ያለምንም መድልኦ የመብቶቻቸው ተጠቃሚዎች ሲሆኑ ብቻ በመሆኑ ነው፡፡ ለዚህ ነው ጉዳዩ የዓለምን ሁሉ ዓይን መሳቡና ፆታዊ መድልኦን አስመልክቶ ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶችና ድንጋጌዎች እንዲወጡ መደረጉ፡፡ በዚህም ብዙዎቹ ዲሞክራሲያዊ ሀገራት ከዓለም አቀፋዊው ስምምነቶች ላይ የተቀዱ ብሄራዊ የሰብዓዊ መብቶችን በህገ መንግሥታቸው ውስጥ ሊደነግጉ ችለዋል፡፡ የኢፌዲሪ ህገ መንግሥትን መሠረት በማድረግ በሀገራችን የሴቷን ህገ መንግሥታዊ መብቶችና ጥቅሞች የሚያስጠብቁ የተለያዩ አስተዳደራዊ፣ የፖሊሲና የህግ ማሻሻያዎች እንዲወጡ ተደርጓል፡፡

በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 34 ላይ እንደተደነገገው፣ ሁለቱም ፆታዎች ያለምንም ልዩነት ጋብቻ የመፈጸምና ልጆች የማፍራት መብት አላቸው፡፡ አንቀጽ 35 ደግሞ በተናጠል ሴቶች ከወንዶች ጋር እኩል መብት እንዳላቸውና በበታችነትና በልዩነት በመታየታቸው የደረሰባቸው ኋላ ቀር የታሪክ ቅርስ እንዲታረምላቸው ከመደረጉም በላይ በተጨማሪ የድጋፍ እርምጃዎች ተጠቃሚ የመሆን መብት እንዳላቸው ይደነግጋል፡፡  የዜጎች ህገ መንግሥታዊ መብቶችና ጥቅሞች ሳይሸራረፉ እንዲጠበቁና ዜጎችም የመብታቸው ሙሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚቆጣጠሩ ዲሞክራሲያዊ ተቋማት በአዋጅ እንዲቋቋሙ ደግሞ በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 55 ላይ ተደንግጓል፡፡ ከነዚህ ዲሞክራሲያዊ ተቋማት መካከል የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አንዱ ሲሆን በዜጎች ላይ የሚደርሱ አስተዳደራዊ በደሎችን እንዲቆጣጠር፣ እንዲከታተልና በደል ደርሶ ከተገኘም የመመርመርና የመፍትሄ ሀሳብ የመሻት ሥልጣንና ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ የሴቶችን ህገ መንግሥታዊ መብት ከማስከበር አኳያ በተለየ መልኩ ከፆታ እኩልነት ጋር ተያይዞ የወጡ ህጎች፣ ፖሊሲዎች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎችና አዋጆች ጭምር በሚመለከታቸው አካላት በተገቢው መንገድ እየተፈጸሙ ስለመሆኑ የቁጥጥርና የክትትል ሥራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

ይህ ሁሉ የሚሆነው ባንድ በኩል በሴቶች ላይ የሚደርሱትን አስተዳደራዊ በደሎች በመቅረፍ ሴቶች የመብታቸው ሙሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የሴቶች ተጠቃሚነት ዞሮ ዞሮ ጥቅሙ የመላው ህብረተሰብ በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ በፆታዊ መድልዖ ተጎጂው ሴቷ ብቻ ሳትሆን ህብረተሰቡ በሙሉ በመሆኑ ወንዱም ሴቱም በዚህ አስከፊ ተግባር ላይ በጋራ በመዝመት የሚደርስባቸውን አስተዳደራዊ በደል መቅረፍ ብሎም ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡

 
በራችንን ክፍት የማድረግ አለያም ሲንኳኳ የመክፈት ግዴታ
ረብዕ, 30 April 2014 06:53

የሰዎች ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በተባበሩት መንግስታት ዓለማቀፉ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ አንቀጽ 19 ላይ ተመልክቷል፡፡ መረጃ የማግኘት መብትም ከዚሁ የሚመነጭ ነው፡፡ ይህ መብት ሁሉም ዜጎች የፈለጉትን የማሰብና ያሰቡትንም የመግለጽ መብታቸው እንዲከበርላቸው ያደርጋል፡፡ የመረጃ ነፃነት የማንኛውንም ሰው መረጃ የመፈለግ፣ የመቀበል፣ እና የመስጠት መብቶችን የጠቃልላል፡፡ ይህ ደግሞ በመንግሥት አካላት ዘንድ መረጃን ለመስጠት በሮቻቸውን ክፍት እንዲያደርጉ የሚያስገድድ ድንጋጌ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

በዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ አንቀጽ 19 ላይ እንደተቀመጠው ሁሉ በኢፌዲሪ ህገ መንግሥት አንቀጽ 29 ላይም ይኸው ድንጋጌ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ በዚህ መሠረት ማንኛውም ሰው የፈለገውን አመለካከት የመያዝና ያለምንም ጣልቃ ገብነት ሀሳቡን የመግለጽ መብቱ ተረጋግጧል፡፡ ይህም ሲባል፣ ማንኛውም ሰው ማንኛውንም ዓይነት መረጃ የማግኘት፣ የመቀበልና የማስተላለፍ መብቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ይህንን መረጃ በመረጠው መንገድ፣ ማለትም በቃል፣ በጽሁፍ፣ ወይም በኤሌክትሮኒክ ውጤቶች እንዲሁም በመረጣቸው መንገዶች ሁሉ መቀበልና መስጠት ይቻላል፡፡

በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 መሠረትም የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 ተደንግጓል፡፡ የአዋጁ ክፍል ሦስት አንቀጽ 13 ላይ እንደተጠቀሰው የህዝብ አገልጋይ ተቋማት መረጃ ከመጠየቃቸው በፊት አትመው የማውጣት ግዴታ አለባቸው፡፡ በዚህ መሠረት ህዝባዊ ተቋማቱ መረጃ ከመጠየቃቸው በፊት አስቀድሞ በማዘጋጀት (proactively) መስጠት ማለት ነው፡፡ ሁሉም ተቋማት የውስጥ አሠራራቸውን፣ ተቋማዊ መዋቅራቸውን፣ ፖሊሲያቸውን፣ የኃላፊዎችን የሥራ ድርሻ፣ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት፣ የቅሬታ አሰማም ሂደት፣ መመሪያዎችን፣ ማኑዋሎችን ወዘተ. በማሳተም ለህዝቡ ማሰራጨት አለባቸው፡፡ ይህ ሲሆን ህብረተሰቡ መንግሥታዊ ተቋማት ምን ምን ተግባራት እያከናወኑ እንደሆነ እንዲያውቁ ያስችላል፡፡ ከዚህ ባሻገር ዜጎች በተለያዩ ህዝባዊ ጉዳዮች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸውና የሥራ ኃላፊዎች ደግሞ ተጠያቂነታቸውን እንዲረዱ ያደርጋል፡፡

የመረጃ ነፃነት መብት መረጋገጡ በመንግሥት በኩል ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲኖር ሲያደርግ በህዝቡ በኩል ድግሞ መንግሥታዊ ተቋማት ላይ ያላቸው አመኔታና ተቀባይነት እንዲያድግ በማድረግ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ ስለሆነም በማንኛውም መንግሥታዊ አካል ዘንድ የሚገኙ መረጃዎች በመረጃ ነፃነት ህጉ መሠረት በምስጢር ከሚጠበቁ ውስን መረጃዎች በስተቀር ከመጠየቃቸው በፊት ለህብረተሰቡ መገለጽ ይኖርባቸዋል፡፡

የመንግሥት አካላት መረጃ የሚሰጡበት ሁለተኛው ግዴታ መረጃ በተጠየቁበት ጊዜ የመስጠት (reactive) ነው፡፡ ይህም ሲባል ተቋማቱ ከህዝቡ የሚቀርብላቸውን የመረጃ ጥያቄ የመቀበልና ለጥያቄውም ተገቢውን ምላሽ የመስጠት ግዴታ አለባቸው ማለት ነው፡፡ ማንኛውም መረጃ ፈላጊ የሚመለከታቸው ኃላፊዎች ዘንድ በመቅረብ ስለ ተቋማቱ ኃላፊነትና ተግባራት እንዲሁም በመስሪያ ቤቱ የሚገኙ ሰነዶችን የመጠየቅ መብት አለው፡፡ በዚህ መልኩ የሚመለከታቸው ኃላፊዎች በቀረበው የመረጃ ጥያቄ መሠረት ዋና ሰነዶችን ወይም ኮፒዎችን በማቅረብ መረጃ የመስጠት ኃላፊነት እንዳለባቸው በዚሁ አዋጅ ላይ ተጠቅሷል፡፡ መረጃ ፈላጊው የጠየቀው መረጃ በአዋጁ ላይ ውስን ክልከላ ከተደረገባቸው መረጃዎች የሚመደብ ከሆነ ኃላፊዎቹ መረጃውን ለመስጠት አይገደዱም፡፡ ሆኖም መረጃ ፈላጊው ይህን መሰል ጥያቄ የማቅረብ መብት ያለው ሲሆን ኃላፊዎችም መረጃው የማይሰጥበትን ምክንያት የማስረዳት ኃላፊነት አለባቸው፡፡

እነዚህ ሁለት የመረጃ መስጫ መንገዶች ማለትም ቅድመ ጥያቄ (proactive) መረጃ ስርጭትና ሲጠየቁ መረጃ የማቅረብ (reactive) ግዴታዎች የመረጃ ነፃነት ህጉ በአግባቡ እንዲተገበር ያደርጋሉ፡፡ ይህ ተግባር ተከናውኖ ሲገኝ በመንግሥት በኩል ተጠያቂነትና ግልጽነት እንዲሰፍንና ህዝቡም በመንግሥት ላይ ያለው አመኔታ እየጎለበተ እንዲሄድ ለማድረግ ያስችላል፡፡ ባጠቃላይ መረጃ የማግኘት መብት የተመሠረተው የመንግሥት አካላት የመንግሥት አገልጋይ ናቸው በሚል መርህ መሠረት በመሆኑ ሁሉም የመንግሥት ተቋማት በሮቻቸውን ለመረጃ ፈላጊዎች ክፍት የማድረግና ሲጠየቁም ትክክለኛ፣ ወቅታዊና ተጨባጭ የሆነ ምላሽ የመስጠት ህገ መንግሥታዊ ግዴታ እንዳለባቸው ሊታወቅ ይገባል፡፡

መጨረሻ የተሻሻለው በ አርብ, 31 October 2014 08:40
 
<< Start < Prev 1 2 Next > End >>

Page 1 of 2