FAQ FAQ

በተደጋጋሚ ለተቋሙ የሚቀርቡ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው(FAQ)

1  በተቋሙ የማይታዩ ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው?

ተቋሙ ፡-

  • በሕዝብ ምርጫ የተቋቋሙ ምክር ቤቶች በሕግ አውጭነታቸው የሚሰጧቸው ውሳኔዎችን፤
  • በፍርድ ቤቶች ወይም በህግ የመዳኘት ስልጣን በተሰጣቸው አካላት በመታየት ላይ ያሉ ጉዳዩች ወይም የታዩና ውሳኔ የተሰጠባቸው ጉዳዩችን፤
  •  በፌደራል ዋና ኦዲተር ወይም በክልል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት በመታየት ላይ ያሉ እና የመጨረሻ ውሳኔ ያገኙ ጉዳዮችን፤ወይም
  • በመከላከያ ሠራዊትና በፖሊስ ክፍሎች የሚሰጡ የፀጥታ ወይም የሀገር መከላከል ጉዳዮችን በሚመለከት የሚሰጡ ውሳኔዎችን የመመርመር ስልጣን የለውም፡፡

2.ተቋሙ በሴቶች፤ ሕፃናት፤ አካል ጉዳተኞችና አረጋዊያን መብቶች ላይ ምን እየሰራ ነው?

ተቋሙ ከተቋቋመበት  ዕለት ጀምሮ የእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች አስተዳደራዊ መብቶች በአስፈፃሚ አካላት መከበራቸውን ለማረጋገጥሴቶች፤ ሕፃናት ፤አካል ጉዳተኞችና አረጋዊያን ዕንባ ጠባቂና የስራ ሂደት ተቋቁሞለት በርካታ የቁጥጥር፤ የጥናትና የግንዛቤ ማሳደግ ተግባራትን እየሰራ ይገኛል፡፡

3.ለተቋሙ ቅሬታ ማቅረብ የሚቻለው በየትኞች መስሪያ ቤቶች በተፈፀሙ የአስተዳደር በደሎች ላይ ነው?

በመንግስትመስሪያቤቶች ማለትም ሚኒስቴር፤ኮሚሽን፤ባለስልጣን፤ኤጀንሲ፤ኢንስቲትዩት፤ወይም ማናቸውም ሌላ የመንግስት መስሪያ ቤትና የመንግስት የልማት ድርጅት ማለትም በመንግስት ባለቤትነት ስር የሚገኝ የማምረቻ፤የማከፋፈያ፤አገልግሎት ሰጭ ወይም ሌላ ዓይነት ድርጅቶች በሚፈፀሙ አስተዳደራዊ በደሎች ላይ ነው፡፡

 

4. ለተቋሙ የሚቀርቡት ጉዳዮች ዋነኛ ምክንያቶች፡-

ተቋሙ የመመርመር ስልጣን የተሰጠው በአስፈፃሚ አካል የሚደርሱ አስተዳደራዊ በደሎች ነው፡፡እነዚህ በደሎች የሚፈጸሙት ለጉዳዩ በቂ ትኩረት ባለመስጠት፤በቸልተኝነት ወይም በግዴለሽነት፤ውሳኔ በማዘግየት፤በወገንተኝነት፤በአድሎአዊነት፤መረጃ ባለመስጠት ወይም የተሳሳተ መረጃ በመስጠት፤በወቅቱ ካለማሳወቅ፤ሚዛናዊ ካለመሆን፤በትህትና ጉድለት፤ምክንያታዊ ካለመሆን፤በዘፈቀደ በመስራት፤በብቃት ማነስና በመሳሰሉት ምክንያቶች በደሎች በአስፈፃሚ አካላትሲፈፀሙ ለተቋሙ አቤት ማለት ይቻላል፡፡   

5.ለተቋሙ አቤቱታ ማቅረብ ያለበት ማን ነው?

ማንኛውም በአስፈፃሚ አካላት አስተዳደራዊ በደል የደረሰበት በራሱ ወይም በተወካይ ማቅረብ ይችላል፡፡

6.የሚቀርቡ አቤቱታዎችን ለመመርመር ክፍያው እንዴት ነው?

የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አገልግሎት በነጻ ነው፤ምንም ዓይነት ክፍያ አይጠይቅም፡፡

7.ተቋሙ ስሙ እንዳይገለጥ የሚፈልግ አቤቱታ አቅራቢን ያስተናግዳል ወይ?

የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ግለሰቡን ማንነት ሳይሆን የጉዳዩን ምንነት ነው የሚፈልገው፡፡ነገር ግን ጉዳዩን ለመመርመርና የመፍትሄ ሀሳብ ለማቅረብ የሚያስችል መረጃ በተቻለ ተያይዞ እንዲቀርብ ይፈለጋል፡፤

8.አቤቱታ እንዴት ማቅረብ ይቻላል?

አቤቱታ አቀራረቡ ቀላል ነው፡፡በስልክ  በሶስተኛ ሰው በፖስታ በሌላ ተወካይ ማቅረብ ቢቻልም የባለጉዳዩ መገኘት የመፍትሄ ሀሳቡን ከጥፋት ፈጻሚው ጋር ለማግባባት ያግዛል፡፡በተጨማሪም ከተቻለ ማንኛውንም አስፈላጊ መረጃዎች ኮፒ በመያዝ ነው በሌላ ሰው አቤቱታ ማቅረብ የሚቻለው፡፡ በምርመራ ሂደት ግን ባለጉዳዩ መቅረብና መነጋገር ይኖርበታል፡፡

9.በአቤቱታ የሚካተቱ ጉዳዮች ምን ምን ናቸው?

እንደ ጉዳዩ ክብደትን ቅለት ይወሰናል፡፡ከተቻለ በተጨባጭ መረጃ ላይ የተመሰረተ በደሉ የተፈጸመበት ቦታ፤ጊዜ፤ በደሉን ያደረሰው አካል፤ ቅሬታ የቀረበባቸው ከአካሉ ቀጥሎ ያሉ አደረጃጀቶች፤ በመጨረሻ እንባ ጠባቂ ምን ሊያደርግላቸው እንደሚፈልጉ በዝርዝር መቅረብ አለበት፡፡

10.የምርመራ ሂደት ምን ያህል ጊዜ ይወስዳል?

ተቋሙ በፍጥነት ጉዳዩ መፍትሄ እንዲያገኝ ጥረት ያደርጋል ነገር ግን የጉዳዩ ዓይነትና የመረጃ አቅርቦት ይወስኑታል፡፤በጣም ቀላል ከሆነ በሳምንት፤በአስቸኳይ ከሆነ በቀናት  መረጃዎችን ማጠናቀር የሚጠይቅ ከሆነ በወራት ሊያልቅ ይችላል፡፡ጉዳዩ ያለበትን ደረጃ በየወቅቱ ለአቤቱታ አቅራቢው በተለያዩ መንገዶች እናሳውቃለን፡፡  

11.ተቋሙን ይግባኝ መጠየቅ ይቻላል ወይ?

ማንኛውም አቤቱታ አቅራቢ ወይም አስፈጻሚ አካል የተቋሙኃላፊ ወይም  መርማሪ በሰጠው የምርመራ ውጤትና የመፍትሄ ሀሳብ ወይም ውሳኔ ላይ ቅሬታ ያለው ከሆነ የምርመራ  ውጤትና የመፍትሄ ሀሳብ ወይም ውሳኔ በፅሁፍ  ከደረሰው ጊዜ አንስቶ በ30 ቀናት ውስጥ ቤደረጃው ከዳይሬክተር ጀምሮ እስከ ዋና ዕንባ ጠባቂው የማቅረብ መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡  

12.ተቋሙ የሚያስቀጣው ቅጣት አለ  ወይ?

ማንኛውም ሰው በተቋሙ መጥሪያ ደርሶት ወይም በሌላ ሁኔታ ተጠርቶ ካልቀረበ ወይም ለምርመራ፤ወይም ለቁጥጥር ስራ ማስረጃዎችን ወይም ሰነዶችን እንዲያቀርብ ተጠይቆ ተቋሙ በጠየቀው ጊዜ ገደብ ውስጥ የማያቀርብ ወይም የምርመራ ወይም የቁጥጥር ስራ እንዳይሰራእንቅፋት የሆነ፤ወይም ምስክሮች ወይም አቤቱታ አቅራቢዎች ለተቋሙ ስራ በማናቸውም መንገድ በተባበሩ ወገኞች ላይ ጥቃት ያደረሰ ወይም ያለ በቂ ምክንያት በተቋሙ በቀረበ የምርመራ ውጤትና መፍትሄወይም የቁጥጥር ውጤት መሰረት እርምት እርምጃ በ30 ቀናት ውስት ያልወሰደ እንደሆነ ከአምስት ዓመት እስከ ሰባት ዓመት በሚደርስ እስራት ወይም በብር 10 ሺ(አስር ሺ ብር ) የገንዘብ መቀጮ ወይም በሁለቱም ይቀጣል፡፡

13.ለተቋሙ የሚቀርብ አቤቱታ በስም ማጥፋት ያስጠይቃል ወይ?

ለተቋሙ የሚቀርብ አቤቱታ በስም ማጥፋት አያስጠይቅም፡፡በተመሳሳይተቋሙ ስለሚያካሂደው ምርመራ ውጤት ለምክር ቤቱ የሚያቀርበው ሪፖርት ወይም በመገናኛ ብዙሀን በሚሰጠው ይፋዊ መግለጫ ወይም ስራውን በማስመልከት በሚያደርገው ሌላ ዓይነት መጻጻፍ በስም ማጥፋት የሚያስጠይቅ አይሆንም፡፡