Web Content Display Web Content Display

የዕንባ ጠባቂ ተቋም በአፍሪካ

የተለያዩ ፅሁፎች እንደሚያስረዱት እንባ ጠባቂ ማለት በመንግስት ወይም በተወካዮች ምክር ቤት የሚሾም ሆኖ ከዜጎች በመንግስት አስተዳደር ላይ የሚቀርቡለትን አቤቱታዎችን በመቀበልና በመመርመር የህዝብን ጥቅም ለማስከበር የሚቆም ነው፡፡

ዶክተር ሙኮሮ ኦክፖሙቪር ዊክፒዲያ ኢንሳይክሎፒዲያ 2007ን ጠቅሶ እንደፃፈው “እንባ ጠባቂ መጀመሪያ የተቋቋመው በስዊድን ሀገር ሲሆን ጊዜውም 1808 እ.ኤ.አ. ነበር፡፡ ‘ombudsman’ የሚለው ቃል ከስዊድንኛ ቃል የተገኘ ሲሆን በስዊድንኛ ‘ombudsman’ ወደ  እንግሊዝኛ ሲተረጎም  representative ማለት ነው፡፡ የተቋቋመውም የዜጎችን መብት ለመጠበቅ ከመንግስት ገለልተኛ የሆነ ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ በማቋቋም ነበር ፡፡” ይላል፡፡

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ተቋሙ በአለም ዓቀፍ ደረጃ ቀጥሎም በአፍሪካ የዜጎችን መብት ለማስጠበቅ መንቀሳቀስ የጀመረ ሲሆን ተግባሩን አስመልክቶ ዶክተር ሙኮሮ ኦክፖሙቪር የእንባ ጠባቂ አተገባበር በአፍሪካ መንግስታት የህዝብ አገልግሎት በሚለው ጥናቱ እንደገለፀው “ተቋሙ ተግባሩ በአለም አቀፍ ደረጃ ተመሳሳይ ሲሆን በዋናነት፡-

 • የዜጎችን መብት መጠበቅ
 • የመንግስት ባለስልጣናት የስልጣን አላግባብ መጠቀምን የመቆጣጠር
 • መመርመር፣ብልሹ አሰራሮችን ማጋለጥና ህጋዊ ተግባራትን ማበረታታት ነው፡፡” ይላል፡፡

 ከላይ እንደተዘረዘረው የዕንባ ጠባቂ ተቋም በአለም አቀፍ ደረጃ ዋና ተግባራቶቹ ተመሳሳይ ሲሆኑ የዜጎች ህገ መንግስታዊ መብቶችና ጥቅሞች በአስፈፃሚው አካላት እንዲከበሩ፣ የህግ የበላይነትን መሰረት ያደረገ ጥራት፣ቅልጥፍናና ግልፅነት ያለው መልካም የመንግስት አስተዳደር እንዲሰፍን፣ ዜጎች በመንግስት ብልሹ አስተዳደር ተበድለው እንዳይቀሩ መፍትሄ መፈለግ፣ የሰዎች አቤቱታዎችን በመመርመር የማረምና ብልሹ አሰራሮች ሲገኙ የማጋለጥና ህጋዊ ተግባራቶችን የማበረታታት ስራዎችን በማከናወን የሰዎች መብቶች እንዲከበሩ የሚሰራ ተቋም ነው፡፡

  ከዚህ አንፃር ዜጎች ከአስፈፃሚ አካላት ጋር በሚያደርጉት የእለት ተእለት ግንኙነት የሚያጋጥሟቸውን አስተዳደራዊ በደሎች ለይቶ በማውጣት አስፈላጊውን የእርምት እርምጃ እንዲወሰድባቸው ከማድረግ አኳያ የበኩላቸውን ሚና መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡ይህም የሚደርሱባቸው አስተዳደራዊ በደሎችና ኢፍትሀዊ አሰራሮች እንዲታረሙ በማድረግ ግልፅነት ያለውና የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ ከማስቻሉም በላይ የመብቶቻቸው ተጠቃሚ በመሆን የእለት ተለት ኑሯቸውን በተሳካ ሁኔታ ለመምራት የሚያስችላቸው ይሆናል፡፡

  ዜጎች  ከመንግስት አስፈፃሚ አካላት የሚደርስባቸውን አስተዳደራዊ በደሎች ተሸክመው እንዳይቀሩና በቀላሉ ቅሬተቀዎቻቸውን የሚያቀርቡበትና መፍትሄ የሚሹበት ተቋም በማስፈለጉ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በአፍሪካ ደረጃ ተቋቁሞ ወደ ስራ ከገባ ረጅም አመታት ተቆጥረዋል፡፡

ተቋሙ ከ 1965 እ.ኤ.አ. ጀምሮ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ተቋቁሞ ዜጎችን በማገልገል ላይ የሚገኝ ሲሆን ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ያበረከተው አስተዋፅኦ ቢኖርም በአፍሪካ ደረጃ የመንግስት መልካም አስተዳደር እስካለንበት ጊዜ ድረስ በርካታ ጥያቄዎች የሚነሳበት ነው፡፡

ዶክተር ሙኮሮ ኦክፖሙቪር  እንደገለፀው “በአፍሪካ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የተቋቋመው በታንዛኒያ ሲሆን እ.ኤ.አ. 1965 ነበር፡፡ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በአፍሪካ እ.ኤ.አ. በ 1980 በቁጥር ስድስት ብቻ የነበሩ ሲሆን በ 1995 ቁጥራቸው በእጥፍ  አድገዋል፡፡” ይላል፡፡

ይህ የሚያመለክተው ዕንባ ጠባቂ ተቋም በአፍሪካ ተጠያቂነትን በመንግስት አስተዳደርና በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ መሳሪያ ሆኖ ለማስከበር እንዴት እየተስፋፋ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡

“የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በአፍሪካ የመንግስትን አገልግሎት አሰጣጥ መንግስት ራሱን የሚፈትሽበትና ተጠያቂነትን፣ሙስናን መከላከልና ብልሹ አስተዳደርን ለመከላከል ተስፋ የተጣለበት ነው፡፡ ተቋሙ በአፍሪካ ውጤታማነቱ ከሀገር ሀገር የሚለያይ ቢሆንም የተቋሙ መኖር ግን ዜጎችን በመልካም አስተዳደር እጦት እንዳይቸገሩ ሀላፊነት ወስዶ ዜጎችን ለመርዳት ፍላጎት በማንፀባረቁና በመዘጋጀቱ ዜጎች ተጨባጭ ሊባል የሚችል መፍትሄ አግኝተዋል፡፡ ይህ ደግሞ በአፍሪካ የመንግስት ሰራተኞች ዜጎችን በአግባቡና በሚዛናዊነት እንዲያገለግሉ መልእክት ያስተላልፋል፡፡ በሌላ መልኩ ምንም እንኳን ተቋሙ መሰረታዊ ቢሆንም ተቋሙ የቆመለትን መልካም የመንግስት አስተዳደር የማስፈን ግቡን አልመታም፡፡ ምክንያቱም የተጠያቂነትና መልካም አስተዳደር ደረጃው ከፍ አላለምና ነው፡፡” ይላል ዶክተር ሙኮሮ ኦክፖሙቪር

 ከላይ እንደተገለፀው የመንግስት አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ አሁንም በርካታ ችግሮች ያሉበት  ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ በመንግስትና በህዝብ መካከል ሰፊ ክፍተት በመኖሩ ብቻ አይደለም አስተዳደሩ በራሱ ለህግ የበላይነት አለመገዛትና ስልጣንን በአግባቡ መጠቀም አለመቻሉ ነው፡፡

ተቋሙ በአፍሪካ የህዝብ አገልግሎት ፍትሃዊነት ለማስፈን በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ምክንያቱም ሙስናን ለመከላከል፣ ሰብአዊ መብቶችን ለማስጠበቅና ዜጎች በመንግስት አስተደሰደር የሚደርስባቸውን በደል በማገዝና ተበድለው እንዳይቀሩ መፍትሄ በመፈለግ ጥሩ ሚና የሚጫወት በመሆኑ ነው፡፡

እንዲሁም ተቋሙ በዋናነት ከዜጎች የሚቀርቡ አቤቱታዎችን ለማስተናገድ የሚያገለግል ሲሆን የመንግስትን ብልሹ አስተዳደርን መጠየቅ  የሚያስችል ስልጣንም አለው፡፡

ይህን በተመለከተ ዶክተር ሙኮሮ ኦክፖሙቪር ሂል 2000ን ጠቅሶ እንደፃፈው “የተቋሙ አብዛኛው ስራ ብልሹ የመንግስትን  አስተዳደር ለማረም ወኪል ሆኖ የሚሰራ ነው፡፡” ይላል፡፡

          በሀገራችን ኢትዮጵያ

በ1966 ዓ.ም በንጉሰ ነገስት ኀይለ ስላሴ የመንግስት አገዛዝ ዘመን መጨረሻ ላይ ረቂቅ ህገመንግስት የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋምን ለማቋቋም እንደ ህገመንግስት ማሻሻያ ተይዞ የነበረ ቢሆንም የደርግ ወታደራዊ መንግስት ሲተካ በ1979 ዓ.ም በወጣው ህገመንግስት ማሻሻያው የተሰረዘ ሲሆን ከረጅም ጊዜ በኋላ የተቋሙ መኖር አስፈላጊነት ታምኖበት በኢፌድሪ ህገመንግስት አንቀፅ 55/15 በተቀመጠው መሰረት በሀገራችን የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በ አዋጅ ቁጥር 211/1992  ተቋቋመ፡፡  ተቋሙ በተሰጠው ስልጣንና ተግባር መሰረት የዜጎች ህገመንግስታዊ መብቶችና ጥቅሞች በአስፈፃሚው አካላት እንዲከበሩ፣ የህግ የበላይነትን መሰረት ያደረገ ጥራት፣ቅልጥፍናና ግልፅነት ያለው መልካም የመንግስት አስተዳደር እንዲሰፍን ለማድረግ  ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም  የመረጃ ነፃነት አዋጅ ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 590/2000 በክፍል ሶስት ስር የተደነገጉትንና ለተቋሙ የተሰጡ ሀላፊነቶችን ለማስፈፀም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

 

የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ለመልካም አስተዳደር ግንባታ ያለው ሚና

   ..........................................................................................

እንደሚታወቀው መልካም አስተዳደር የተግባር እንጂ የንድፈ ሀሳብ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህም ሲባል የመልካም አስተዳደር ተግባር ከዜጎች የእለት ተለት የኑሮ ሁኔታ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ በመሆኑ በአተገባበሩ ላይ የስልጣኑ ባለቤት የሆነው ህዝብ ቀጥተኛ ተሳታፊ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ይህም ህዝቡ በህገመንግስቱ የተጎናፀፈውን ስልጣን በአግባቡ እንዲጠቀምበት እድል ይሰጣል፡፡

በሀገር ደረጃ የመልካም አስተዳደር ችግር ለመቅረፍ የአስተሳሰብ ለውጥን ከማምጣት ጀምሮ ከላይ እስከታች ድረስ የተሰናሰለ እንቅስቃሴና ተግባር እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ ስለሆነም አስፈፃሚ አካላት ለህዝቡ ተገቢውን አገልግሎት በቅንነትና በተቀላጠፈ መልኩ መስጠት ይገባኛል ብሎ ማመንና መተግበር ያለባቸው ሲሆን ተገልጋዮች ደግሞ አገልግሎት ማግኘት በሚገባቸው ደረጃ እንዲያገኙ ጠያቂ መሆንና የሚጠበቅባቸውን ግዴታ መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በሀገራችን መልካም የመንግስት አስተዳደር ችግር ቁልፍ ጉዳይ መሆኑ እሙን በመሆኑ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የመንግስት አካላትና ህብረተሰቡ እጅ ለእጅ ተያይዘው መስራት ይገባቸዋል፡፡

ይህን አስመልክቶ መልካም አስተዳደር ዛሬም ቀዳሚ ትኩረት በሚል ርእስ አባ መላኩ ሐተታ በፃፉት አንድ ፅሁፍ “የሀገራችን መንግስት መልካም የመንግስት አስተዳደር እንዲሰፍን በርካታ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ለዚህም የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም እንዲሁም የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ችግሮችን እየተከታተሉ በማረም ለመልካም አስተዳደር ግንባታ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ከተቋቋሙ ገለልተኛ አካላት ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው ፡፡” ይላል፡፡ አያይዞም “ቁልፍ የዴሞክራሲ ማስፈኛ ተቋም ከሆኑት ውስጥ እንደ የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ያሉትን  በአግባቡ በመጠቀምና የሚፈጠሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በማሳወቅ ለመልካም አስተዳደር እመርታ መትጋት  ከማንኛውም ዜጋ የሚጠበቅ ተግባር ነው ፡፡” ይላል፡፡

ከላይ በተጠቀሰው አንቀፅ የምንረዳው የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ለመልካም የመንግስት አስተዳደር ግንባታ ያለውን ሚና የሚያሳይና ህዝቡ ደግሞ የሚደርስበትን አስተዳደራዊ በደሎችን ይዞ ወደ ተቋሙ በመምጣት የመፍትሄ ሀሳብ ማግኘት እንደሚገባው ነው፡፡ ይህን ስንል የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የተቋቋመለት አላማ የሰዎችን ህገመንግስታዊ መብቶችና ጥቅሞች በአስፈፃሚው አካላት እንዲከበሩ የህግ የበላይነትን መሰረት ያደረገ ጥራት ፣ቅልጥፍናና ግልፅነት ያለው መልካም የመንግስት አስተዳደር እንዲሰፍን ማድረግ በመሆኑ ተቋሙ በደል የደረሰባቸውን ዜጎች ተጎድተው እናዳይቀሩ ቅሬታ የሚያሰሙበትና በቀላሉ መፍትሄ የሚያገኙበት የህግ አውጪው አካል ሆኖ የሚያገለግል ህገመንግስታዊ ተቋም መሆኑ ነው፡፡

በሌላ በኩል መልካም አስተዳደር ስንል መንግስታዊ ተቋማት ለዜጎች የሚሰጡትን አገልግሎትና መንግስታዊ ሀብቶችን እንዴት እንደሚተቀሙ የሚያሳይ ሲሆን አስተዳደር ማለት ደግሞ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደትና ውሳኔዎች እንዴት ተግባራዊ እንደሚደረጉ የሚያሳይ ሀሳብ አካቶ የያዘ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መልካም አስተዳደር የመንግስት ውሳኔ አሰጣጥ ዝግጁነት ከውጤታማነት፣ከአሳታፊነትና ከግልፀኝነት አንፃር የሚያሣይና ይህም በመንግስት አስፈፃሚ አካላት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታትና የተሻለ አገልግሎት የመስጠት ዝግጁነት ነው፡፡

ከዚህ አንፃር የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ከተቋቋመበት አላማና በተሰጠው ስልጣን መሰረት በተደጋጋሚ የሚያጋጥሙ መልካም የመንግስት አስተዳደተር ችግሮች የቁጥጥርና ክትትል ስራዎችን በማካሄድ፣ ቅሬታዎችን በመመርመርና የመፍትሄ ሀሳብ በመስጠት ፣ ጥናቶችን በማካሄድ ለመልካም የመንግስት አስተዳደር ግንባታ የተጣለበትን ሀላፊነት በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህም ጎን ለጎን አስፈፃሚ አካላት የሚያወጧቸው አሰተዳደራዊ መመሪያዎች፣ የሚሰጧቸው ውሳኔዎች እና አሰራሮች የዜጎችን ህገመንግስታዊ መብቶችና ጥቅሞች የማይቃረኑ መሆናቸውን የመቆጣጠር እንዲሁም አስፈፃሚ አካላት ስራቸውን በህግ መሰረት የሚያከናውኑ መሆኑን የማረጋገጥና አስተዳደራዊ ጥፋቶችን የማረም ተግባራትን በማከናወን ላይ የሚገኝ ሲሆን ለወደፊቱም  ከአስፈፃሚውና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር  በመተባበር ሀላፊነቱን የሚወጣ ይሆናል፡፡

 

     የህፃናት መብቶች አከባበር ከዕንባ ጠባቂ ተቋም አንፃር

በአብዛኛው ጊዜ ህፃናት በህብረተሰቡ ውስጥ የደህንነት ጥበቃ የሚያስፈልጋቸውና ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡እነዚህ የነገው ሀገር ተረካቢ የሆኑትን ህፃናት መብትና ፍላጎት ማስከበር ከያንዳንዱ ግለሰብ አንስቶ እስከ መንግስት ድረስ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ የህፃናት መብቶችና ጥቅሞች እንዲጠበቁ ብሎም እንዲረጋገጡ ለማድረግ ከጉልበት ብዝበዛ፣ ከጭካኔ ፣ችላ ከማለትና ከግዴለሽነት ለመከላከልና ወላጅ አልባ ህፃናትን ባካተተ መልኩ ተገቢውን ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡

በተለይ ህፃናት ለመብቶቻቸውና ጥቅሞቻቸው መከራከር ስለማይችሉ በጣም ተጋላጭ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በህፃናት መብቶች ዙሪያ የሚሰሩ የተለያዩ ተቋማትንና አደረጃጀቶችን  በመጠቀም ህጋዊና ህገመንግስታዊ መብቶቻቸውን ማስከበር ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ነው፡፡በተጨማሪም በአብዛኛው ጊዜ የህይወት ክህሎታቸው አነስተኛ በመሆኑ የተዘረጋውን ስርዓት መጠቀምም ሆነ የሚደርስባቸውን በደሎች ፍርድ ቤት መክሰስና ለህዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አቤቱታ ማቅረብ ስለማይችሉ ወኪል ያስፈልጋቸዋል፡፡

Canadian center of science and education ባሳተመው ጆርናል ቁጥር 8 እነደሚያሳየው “ ሀገራት የጥቂቶችንና የህፃናት መብትና ፍላጎቶች ጋር የተያያዙ ህጎች ማክበር አለባቸው ምክንያቱም ህፃናት በጣም ተጋላጭና በቂ የህይወት ልምድ የሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በመሆናቸውና መብቶቻቸውንና ፍላጎታቸውን ማስከበር የማይችሉ በመሆናቸው ነው” በማለት ያስቀምጣል፡፡ ይህም ሲባል ወላጅ አልባና  የቤተሰብ ጥበቃ የሌላቸው፣ አካል ጉዳተኛና በተለያየ ማህበረሰብ ውስጥ የሚኖሩ ህፃናትን በሙሉ እንደሚያካትት ጆርናሉ ያትታል ፡፡ ከዚህ አንፃር በሀገር ደረጃና በተቋሙ የህፃናት መብት አጠባበቅ አንፃር እየተሰሩ ያሉ ስራዎች በአጭሩ ሲታዩ፡-

       የህፃናት መብት አጠባበቅ በሀገራችን እንደማሳያ

የኢፌድሪ ህገመንግስት የህፃናትን ሁለንተናዊ መብቶች ሊያስከብሩ የሚችሉ የህግ ማዕቀፎችንና መዋቅሮችን አመቻችቷል፡፡ በህገ መንግስታችን አንቀፅ 36 የህፃናት መብቶች በተመለከተ በዝርዝር ተደንግጓል፡፡ ሆኖም በህፃናት ላይ የሚፈፀሙ አስተዳደራዊ በደሎች አሁንም አልተቀረፉም፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋምም የሴቶች ህፃናት አካልጉዳተኞችና አረጋዊያን ዳይሬክቶሬት የስልጠና ማኑዋል በህፃናት ላይ የሚፈፀሙ አስተዳደራዊ በደሎች አመላካቾች ብለው ከጠቀሷቸው መሀከል የሚከተሉትን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

 1. በህፃናት ላይ ጠለፋ፣አስገድዶ መድፈር፣አካላዊ ቅጣት፣ግርዛት፣ የብልት ትልተላ ወዘተ የመሳሰሉ ድርጊቶች በሚፈፀሙበት ጊዜ በቸልታና በምንአገባኝ ዓይነት መመልከት፣
 2. በህፃናት ህገ-ወጥ ዝውውር ላይ የተሰማሩ ተቋማትን አለመከታተል፣ አለመቆጣጠርና ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ አለመውሰድ፣
 3. በህፃናት የጉልበት ብዝበዛ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችንና ተቋሞችን አለመከታተል፣ አለመቆጣጠርና ተገቢውን ግጋዊ እርምጃ አለመውሰድ
 4. በህፃናት ዙሪያ የወጡ የህፃናት መብቶች ኮንቬንሽንና የደህንነት ቻርተሮችን እንዲሁም በህፃናት ዙሪያ ሀገሪቷ ያወጣቻቸው ፖሊሲዎች፣ፕሮግራሞችና ህጎች ተግባዋዊ አለማድረግ፣
 5. ህፃናት ተገቢውን የክትባትና ሌሎች የጤና አገልግሎቶች እንዲያገኙ አለማድረግና በጤና ተቋማት ለህፃናት ቅድሚያ አለመስጠት፡፡ የሚሉት ማሳያ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ይህንን የህፃናት ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት የተለያዩ ሀገራት መንግስታት የህፃናት መብት ማስከበሪያ አማራጭ በመሆን የሚያገለግል የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አቋቁመዋል፡፡

የዚህ ተቋም መቋቋም ፋይዳው የመንግስት ለህፃናት መብት መከበር ግዴታ የሚወጣ መሆኑን በማስረጃነት ለማሳየት ብቻ ሳይሆን የመብቱ ተደራሽ መሆን የመንግስት ሀላፊነት በመሆኑና ግዴታውንም መወጣት ስላለበት ነው፡፡

         የህፃና መብት ገፅታዎች በዕንባ ጠባቂ ተቋም

የዕንባ ጠባቂ ተቋም ተግባር የአስተዳደር በደል የደረሰባቸው አቤት ባዮች መብታቸውን እንዲያገኙ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን መብት የማስከበር ስልጣንም ተሰጥቶታል፡፡ ተቋሙ ከተቋቋመባቸው አላማዎች አንዱ የህፃናትን መብት ለማስከበር አማራጭ ስርዓት ለመፍጠርም ጭምር ነው፡፡ ይህም የህፃናትን መብት ህጋዊ ጥበቃ ለማሻሻልና መብትና ፍላጎታቸውን በተጨባጭ ለማስከበር የሚጠቅም ሲሆን እንዲሁም ለሰፊው ህዝብ አስተዳደራዊ በደል ለመከላከል የቆመ ነው፡፡

ተቋሙ ባለፉት ዓመታት የህፃናት መብቶች እንዲከበሩ ብሎም እንዲረጋገጡ ለማድረግ አስፈፃሚ አካላትን በመቆጣጠር፣ በአስፈላጊ ጉዳዮች ላይ ምርመራ በማድረግ፣ ጥናቶችንና ቁጥጥሮችን በመስራት የተሻሻለ የትምህርት፣ የጤናና ማህበራዊ አገልግሎቶች የማሳደግ ሀላፊነትና ጥበቃ የማድረግ የበኩሉን ሚና ሲጫወት ቆይቷል፡፡ አሁንም በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡ እንዲሁም መብቶቻቸውንና ጥቅሞቻቸው እንዲጠበቁ በተለያዩ የሚዲያ ዘዴዎች አማካኝነት የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ ተግባራት አከናውኗል፡፡

     ህፃናትን አስመልክቶ የተቋሙ ስልጣንና ተግባራት

 • በተለያዩ የህፃናትጉዳዮች ላይ ምርመራ የማድረግ፣
 • የህፃናት መብት ተጥሶ ሲገኝ ቁጥጥር ማድረግ፣
 • በህፃናት ላይ የሚፈፀሙ የአስተዳደር በደሎችን ለመከላከል የሚያግዝ ጥናት ማካሄድ፣
 • የህፃናት መብት እንዳይጣስ በሚወጡ ህጎች ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ምክረ ሀሳብ ማቅረብ፣
 • በህፃናት ላይ የሚፈፀሙ አስተዳደራዊ በደሎችን ለመከላከል የህፃናት ፓርላማዎችን ማቋቋምና ማጠናከር፣
 • የህፃናት የመልካም አሰተዳደር ፎረም ማቋቋምና መጠቀምን ያካትታል፡፡

በአጠቃላይ ህፃናት በእድሜያቸው ጨቅላነትና ማህበረሰቡ በህፃናት ላይ ባለው የተዛባ አመለካከት ምክንያት ለተለያዩ በደሎችና ጥቃቶች እንዳይጋለጡ የህፃናት መብቶችን ለማስከበርና ጥበቃ ለማድረግ ህግ ግዴታ የጣለባቸው አካላት ማለትም ወላጅ፣አሳዳጊዎች፣ ማህበረሰቡንና መንግስት የህፃናትን ጥቅሞችና ፍላጎቶች ማሟላት፣ መብታቸውን የማስከበርና የማክበር ሀላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በአለም አቀፍ የህፃናት መብቶች ኮንቬንሽን ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው በየደረጃው የሚገኙ መንግስታዊ ፍርድ ቤቶች፣ የአስተዳደር እርከኖችና ማህበረሰቡ በህፃናት ላይ የሚወስዷቸውን እርምጃዎች የህፃናትን ጥቅሞችና ፍላጎቶች ማሟላት፣ መብታቸውን የማክበርና የማስከበር ሀላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡

የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋምም በተሰጠው ስልጣንና ሀላፊነት መሰረት በህፃናት ላይ የሚፈፀሙ አስተዳደራዊ በደሎችን በመከላከልና በማረም ረገድ መፍትሄ የመሻት ተግባሩን አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡  

       

         የቅሬታ አቀራረብና አፈታት በዕንባ ጠባቂ ተቋም

      የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በተሸሻለው አዋጅ ቁጥር 1142/2011 የተቋቋመና አላማውም በህግ የተደነገጉ የሰውች መብቶችና ጥቅሞች በመንግስት አስፈፃሚ አካላት መከበራቸውን በማረጋገጥ የህግ የበላይነትን መሰረት ያደረገ ጥራት፣ቅልጥፍናና ግልፅነት ያለው መልካም የመንግስት አስተዳደር እንዲሰፍን ማድረግ ነው፡፡

      ተቋሙ አላማውን ለማሳካት አስፈፃሚ አካላት የሚያወጧቸውን አስተዳደራዊ መመሪያዎች፣የሚሰጧቸው ውሳኔዎችና አሰራሮች የሰዎች ህገመንግስታዊ መብቶችና ጥቅሞችን የማይቃረኑ መሆናቸውን መቆጣጠር፣ አስተዳደራዊ ጥፋትን አስመልክቶ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን በመቀበልና በመመርመር የተሸለ የመንግስት አስተዳደር እንዲሰፍን ነባር ህጎች እንዲሻሻሉ ወይም ፖሊሲዎች እንዲቀየሱ የማሳሰብ ስልጣንና ተግባር ተሰጥቶታል፡፡

       በዚሁ መሰረት አስተዳደራዊ ጥፋትን አስመልክቶ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ለመቀበል፣ለመመርመርና ከምርመራ በኋላ ያሉ ሁኔታዎችን በተመለከተ የሚከተሉትን ነጥቦችን መመልከት ይቻላልል፡፡

አቤቱታ የሚቀርብበት ሁኔታ       

 • አቤቱታ የሚቀርበው መብቴ ተጥሶብኛል በሚል ሰው ወይም ሶስተኛ ወግ ሊቀርብ ይችላል፡፡
 • እንደ ተፈፀመው የአስተዳደር በደል ክብደት ተቋሙ የአመልካቹ ማንንት ሳይገልፅ የሚቀርቡለትን አቤቱታዎች ሊቀበል ይችላል፡፡
 • ማንኛውም ሰው ለደረሰበት የአስተዳደር በደል ለተቋሙ አቤቱታ ከማቅረቡ በፊት አግባብነት ላላቸው አካላት ደረጃውን ጠብቆ ቅሬታውን የማቅረብ እና ውሳኔ የማግኘት ወይም በተወሰነው የጊዜ ገደብ ውስጥ ውሳኔ ያላገኘ መሆን ይኖርበታል፡፡

 

በቋሙ ተቀባይነት ስለማይኖራቸው አቤቱታዎች

 • በህዝብ ምርጫ የተቋቋሙ ምክር ቤቶች በህግ አውጪነታቸው የሚሰጧቸው ውሳኔዎችን፣
 • በፍርድ ቤቶች ወይም በህግ የመዳኘት ስልጣን በተሰጣቸው አካላት በመታየት ላይ ያሉ ጉዳዮች ወይም የታዩና ውሳኔ የተሰጠባቸው ጉዳዮችን፣
 • በፌደራል ዋና ኦዲተር ወይም በክልል ዋና ኦዲትር መስሪያ ቤት በመታየት ላይ ያሉ እና የመጨረሻ ውሳኔ ያገኙ ጉዳዮችን ወይም በመከላከያ ሰራዊትና በፖሊስ ክፍሎች የሚሰጡ የፀጥታ ወይም የሀገር መከላከል ጉዳዮችን በሚመለከት የሚሰጡ ውሳኔዎችን፡፡

  

 

 

በድርድር ለመፍታት ስለሚቻልባቸው ሁኔታዎች

አቤቱታን በድርድር ለመፍታት ከሚቻልባቸው ሁኔታዎች ውስጥ የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል

 • ከአቤት ባይ ጋር በጉዳዩ ላይ ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር
 • ከተተሪ መስሪያ ቤት ጋር በጉዳዩ ላይ ፍቃደኝነት መኖሩ ስረጋገጥ
 • በተጠሪና በአቤት ባይ መካከል በተገኘው ፍቃድ መሰረት ቃለጉባኤ በመያዝ የማስማማት ስራወን በማከናወን
 • ጉዳዩ በስምምነት ካለቀ የስምምነቱ ፍሬ ሀሳብ በመዘርዘር ሁለቱ ወገኖች እንዲያኖሩ በማድረግ

     ማስረጃዎች እንዲቀርቡ ስለማድረግ

ተቋሙ አሰፈላጊ ማጣሪያዎችን ለማካሄድ በቂ በሆነ ጊዜ ውስጥ፡-

 • ተመርማሪዎች ለጥያቄ እንዲቀርቡ ወይም መልስ እንዲሰጡ፣
 • ምስክሮች ቀርበው ቃላቸውን እንዲሰጡ፣
 • ለጉዳዩ ጠቃሚ የሆነ ማስረጃ የያዘ ማንኛውም ሰው ይህን ማስረጃ እንዲያቀርብ ማድረግ ይችላል፡፡

        መፍትሄ ስለመስጠት

 • ተቋሙ የቀረበለትን አቤቱታ በስምምነት ለመጨረስ የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል፡፡
 • የምርመራውን ውጤት ከነመፍትሄ ሀሳቡ ለሚመለከተው አካል በላይ ሀላፊ በፅሁፍ ያቀርባል፡፡
 • ተቋሙ የሚሰጠው የመፍትሄ ሀሳብ ለተፈፀመው የአስተዳደር በደል ምክንያት የሆነ ድርጊት ወይም አሰራር እንዲቆም ወይም ስለበደሉ ምክንያት የሆነ መመሪያ ቀሪ እንዲሆንና  የተፈፀመው የአስተዳደር በደል እንዲታረም ወይም ተገቢ የሆነ ማንኛውም ሌላ እርምጃ እንዲወሰድ በግልፅ የሚያመለክት ይሆናል፡፡
 • ተቋሙ የምርመራ ውጤቱን ለአቤቱታ አቅራቢው በፅሁፍ ያሳውቃል፡፡
 • ለተቋሙ የሚቀርቡ አቤቱታዎች ከስድስት ወር ባልበለጠ ጊዜ ውሰጥ ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ምላሽ ያገኛሉ

                የአስፈፃሚ አካላት ግዴታ

ተቋሙ አግባብነት ያላቸውን ሰነዶች ወይም ማስረጃዎች እንዲቀርቡ ወይም መልስ እንዲሰጡ ሲጠየቁ የተጠየቀው አካል በተሟላ አኳኋን የማቅረብ ግዴታ አለበት፡፡

አስፈፃሚ አካላት በተቋሙ በቀረበ የምርመራ ውጤትና የመፍትሄ ሀሳብ ላይ በ30 ቀናት ውስጥ የእርምት እርምጃ መውሰድ ግዴታ አለበት፣ የወሰዱትን እርምጃ እና ለመውሰድ ካልቻለ በቂ ምክንያት ካላቸው ይህንኑ በመግለፅ ለህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡

       

 የቅጣት ሁኔታ

1.ማንኛውም ሰው ፡-

 • በተቋሙ መጥሪያ ደርሶት ወይም በሌላ ሁኔታ ተጠርቶ ካልቀረበ ወይም
 • ለምርመራ ወይም ለቁጥጥር ስራ ማስረጃዎችን ወይም ሰነዶችን እንዲያቀርብ ተጠይቆ ተቋሙ በጠየቀው የጊዜ ገደብ ውስጥ የማያቀርብ ወይም
 • የምርመራ ወይም የቁጥጥር ስራ እንዳይሰራ እንቅፋት የሆነ ወይም
 • ምስክሮች ወይም አቤቱታ አቅራቢዎች ወይም ለተቋሙ ስራ በማናቸውም መንገድ በተባበሩ ወገኖች ላይ ጥቃት ያደረሰ ወይም
 • ያለበቂ ምክንያት በተቋሙ በቀረበ የምርመራ ውጤትና መፍትሄ ወይም የቁጥጥር ውጤት መሰረት የእርምት እርምጃ በ 30 ቀናት ውስጥ ያልወሰደ እንደሆነ ከ 5 ዓመት እስከ 7 ዓመት በሚደርስ እስራት ወይም በብር 10000 /አስር ሺህ/ ገንዘብ መቀጮ ወይም በሁለቱም የቀጣል፡፡

  2. በዚህ አንቀፅ ንኡስ አንቀፅ 1 የተዘረዘሩትን ጥፋቶች የፈፀመ ማንኛውም ሰው በህግ         እንዲጠየቅ ተቋሙ በቀጥታ ጉዳዩ ለሚመለከተው አቃቤ ህግ መስሪያ ቤት ድርጊቱን ሪፖርት ከደጋፊ ማስረጃዎች ጋር ያቀርባል፣ ከተቋሙ ትዛዝ የደረሰው አቃቤ ህግ መስሪያ ቤት አግባብ ባለው ህግ መሰረት የወንጀል ክስ ይመሰርታል፡፡

 

 

 

 

የሴቶች ቀን መከበርና የተቋሙ ሚና

የሴቶች ቀን አለም አቀፍ በዓል ሲሆን የሴቶችን ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊና ፖለቲካዊ ስኬቶች የሚዘከርበት ቀን ነው፡፡ በተጨማሪም  ቀኑ የፆታ እኩልነት ተግባራዊነት እንዲፋጠን ጥሪ የሚቀርብበትና አለም አቀፍ የፆታ እኩልነት ቀን ነው፡፡

ዘንድሮም ቀኑ በአለም ለ109ኛ በሀገራችን ደግሞ ለ44ኛ ጊዜ “ የሴቶች ደህንነትና መብት መከበር ለሰላማችንና ለህልውናችን መሰረት ነው” በሚል መሪ ቃል የካቲት 29/2012 ዓ.ም ተከብሯል፡፡

ምንም እንኳ ዛሬ አለም ላይ የሴቶችን እኩልነት በተመለከተ ተጨባጭ የሆነ የአመለካከትና የተግባር ለውጥ ቢኖርም አሁንም ሴቶች ከወንዶች እኩል የስራ ክፍያ አያገኙም፣በንግድም ይሁን በፖለቲካ ከወንዶች እኩል ተሳትፎ የላቸውም፡፡እንዲሁም የትምህርት ሽፋን፣ የሚያገኙት የጤና አገልግሎትና የሚደርስባቸው ፆታዊ ጥቃት ብንመለከት ከወንዶች ጋር እኩል እንዳልሆነ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

 ሴቶች የማህበረሰቡ ግማሽ አካል መሆናቸው የታመነና ያለሴቶች እኩል ተሳትፎ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካ የሚፈለገውን ለውጥ ወይም እድገት ማምጣት እንደማይቻል ግልፅ ነው፡፡ እንዲሁም የሴቶች ደህንነትና መብት መከበር ለሀገር ሰላምና ለህዝብ ህልውና መሰረታዊ መሆኑ ተቀባይነት ያለውና ወደ ተግባር መቀየር ያለበት ቢሆንም ሀገራችንን እነደምሳሌ ብንወስድ እንኳ የእኩልነት ህገመንግስታዊ ድንጋጌዎች ቢኖሩም ሴቶች ለእኩል ስራ እኩል ክፍያ፣ እኩል የስራ ቅጥር፣ የትምህርት እድል፣ የጤና አገልግሎት በተሟላ መልኩ አያገኙም፣ ለፆታዊ ጥቃትና ትንኮሳ የበለጠ ተጋላጭ ሲሆኑ የሚደርስባቸው አስተዳደራዊ በደልም ላቅ ያለ ነው፡፡ የሴቶች የደህንነት መብትና ጥቅሞቻቸው ተከብረው ከወንዶች እኩል ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነታቸው ሳይረጋገጥ ቆይቷል፡፡

ይህን ከግምት በማስገባት የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የሰዎች ህገመንግስታዊ መብቶችና ጥቅሞች በእስፈፃሚው አካላት እንዲከበሩና የህግ የበላይነትን መሰረት ያደረገ ጥራት ቅልጥፍናና ግልፅነት ያለው መልካም የመንግስት አስተዳደር እንዲሰፍን ለማድረግ እንደመስራቱ መጠን ሴቶች የሚደርስባቸውን አስተዳደራዊ በደሎችን ለመከላከል አስፈፃሚ አካላትን በመቆጣጠርና በመከታተል የሚቀርቡለትን አቤቱታዎች ተቀብሎ በመመርመር ለችግሮቹ መፍትሄ ይሰጣል፡፡ በዚህም መሰረት፡-

      ሴቶችን አስመልክቶ ተቋሙ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል

 • ሴቶች ላይ የሚፈፀሙ የአስተዳደር በደሎችን ለመከላከል የሚያግዙ ጥናቶችን ማካሄድ፣
 • አስፈፃሚ አካላት ሴቶችን በተመለከተ የሚያወጧቸው አስተዳደራዊ መመሪያዎች፣የሚሰጧቸው ውሳኔዎችና አሰራሮቻቸው የሴቶችን ህገ-መንግስታዊ መብቶች የማይቃረኑ መሆናቸውን በመቆጣጠር ሀሳብ መስጠት፣
 • አስፈፃሚ አካላትና ህብረተሰቡ ሴቶችን በሚመለከት ያሉት ፖሊሲዎችና ህጎች እንዲገነዘቡ የግንዛቤ ማስፋፊያ ስራ መስራት፣
 • የሴቶች የመልካም አስተዳደር ፎረም ማቋቋምና መጠቀም የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡

በመጨረሻም እያንዳንዱ ሰው ተቋሙ የነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች መብቶችና ጥቅሞች እንዲከበሩ ለማድረግ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ውስጥከተቋሙ ጎን በመቆምና የሴቶችን የወደፊት ህይወት ብሩህ፣እኩል፣ምቹ፣ውጤታማ በማድረግ እንዲሁም ደህንነታቸው፣ መብትና ጥቅሞቻቸው ተከብሮ አስተዳደራዊ በደል እንዳይደርስባቸው በመከላከል ከአስቸጋሪ ህይወት ወጥተው ከፍ ከፍ እንዲሉ በማድረግ ለሰላማችንና ለህልውናችን የበኩላችንን ድርሻ እንድንወጣ ተቋሙ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኮረና ወረርሽኝ ችግሩና በአስፈፃሚ አካላት ላይ ቁጥጥር የማድረግ አስፈላጊነትና ውጤቱ

የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በአዲስ አበባ በተመረጡ ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች ላይ በኮረና ወረርሽኝ ለችግር የተጋለጡ ሴቶች፣ህፃናት፣አካልጉዳተኞችና አረጋዊያን እየተሰጡ ያሉ ሰብአዊ ድጋፎች ግልፅነት ተደራሽነት፣የአሳታፊነትና ፍትሀዊነት በተመለከተ ቁጥጥር አድርጓል፡፡ በቁጥጥሩ የተለዩ የአሰራር ክፍተቶች፣ጠንካራ ጎኖችና መሻሻል የሚገባቸው ጉዳዮችን በመተንተን እንደሚከተለው እናስቃኛችኃለን፡፡

               የቁጥጥሩ አስፈላጊነት

መንግስት በሀገራችን የተከሰተውን የኮረና /የኮቪድ-19/ ወረርሽኝ ተፅእኖ ለመከላከል እና የቫይረሱን መከሰቱን ተከትሎ የወረርሽኙ ስርጭት እያስከተለ ያለውንና ሊያስከትል የሚችለውን ሰብአዊ፣ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውሶችን እንዲሁም የበሽታውን ስርጭት ለመቀነስ ሲባል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ሆኖም አስፈፃሚ አካላቱ ለህብረተሰቡ የሚሰጡ አገልግሎቶች ከወረርሽኙ ጋር ተያይዞ ይበልጥ ተጋላጭና ተጠቂ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች በተለይም ለሴቶች፣፣ህፃናት፣አካልጉዳተኞችና አረጋዊያን እየተሰጠ ያለውን አገልግሎት ጥያቄ እየተነሳባቸው እንደሆነ በተለያዩ መንገዶች እየተገለፀ በመሆኑና ተቋሙ ከተቋቋመባቸው አላማዎች አንዱ የእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች የመልካም አስተዳደር ፍላጎት ምላሽ እንዲያገኙ ለማድረግ ነው፡፡

              ለተጋላጭ ወገኖች ተጠባቂ አገልግሎትና ምላሹ

ቁጥጥሩ በተከናወነባቸው ቦታዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሚያስቀምጠው መሰረት በአናዳንድ ክፍለከተማዎችና ወረዳዎች ለሰራተኛው የጥንቃቄ እርምጃዎችን ባልተሟላበት ወደ ስራ በመግባት በየሴክተሮቹ ከዚህ ቀደም ሲሰጡ የነበሩ አገልግሎቶች እንዲቀጥሉ በሴቶችና የህፃናት ዘርፍ የህፃናት መብትና ደህንነት ተጠብቆ የተሻለ እንክብካቤ እንዲያገኙ የሚያስችሉ ስራዎችን አስመልክቶ የተመደበ በቂ ሀብት ባለመኖሩ ከግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ሴቶችን በልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ የማድረግና የስርዓተፆታ እኩልነትን የማረጋገጥ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ በተደረገ ውይይት ለማወቅ ተችሏል፡፡ እንደችግር ከታዩት መካከል ደግሞ በሴቶችና ህፃናት ዘርፍ በቢሮና በፅ/ቤት ደረጃ በትምህርት ቤቶች ቢደረጉ የምገባ ፕሮግራም ላይ አገልግሎት በመስጠት ተሳታፊ የነበሩና የገቢ ምንጭ የሚያገኙ ሴቶች በኮረና ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው ምገባው በመቆሙ ለችግር እንደተጋለጡ ሴቶችን ተጠቃሚ ለማደረግ ከወረዳዎች ችግረኛ የሆኑትን ድጋፍ ለማድረግ መልምላችሁ ላኩ በሚል ሲጠየቅ ሴቶችን በመለየት ለክፍለ ከተማ ቢላክም ተፈፃሚነቱ ጉልህ ክፍተት ያለበት ነበር፡፡ በተጨማሪም በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ዘርፍ የአካል ጉዳተኞችን፣አረጋዊያንን፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችንና ሌሎች ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመቅረፍ የደሀ ደሀ በሚል ደረጃ በማውጣትና ከነዚህም ውስጥ ምን ያህሉ አረጋዊያንና አካልጉዳተኞች ናቸው በሚል መረጃዎችን አጠናቅሮ ተገቢውን ድጋፍና አገልግሎት እንዲያገኙ እየሰሩ መሆናቸውን መረዳት ቢቻልም አካል ጉዳተኞችና አረጋዊያን በማደራጀት ወደ ስራ በማስገባት ስልጠና ቢሰጥም ሲኦሲ ምዘና ማከናወን አለመቻሉና ካለምዘና ወደስራ መግባት አለመቻሉ እንዲሁም የቦታ ችግር እንቅፋት እንደሆነባቸው በቁጥጥር ለማወቅ ተችሏል፡፡

                  ከታዩ ጠንካሩ ጎኖች መካከል

 • በከተማው ይበልጥ ተጋላጭና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን የህብረተሰብ ክፍሎችን አደረጃጀቶችን በማሳተፍ የደሀ ደሀዎችን በመለየትና ደረጃ በማውጣት መረጃውን በየወረዳው መያዝ መቻሉ፣
 • በኮረና ወረርሽኝ ምክንያት በስራቸውና በኑሮዋቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል ሀብት በከተማ፣በክፍለከተማና በወረዳ እስከ ብሎክ አደረጃጀት ድረስ በመውሰድ ሀብት የማሰባሰብ ስራ እየተሰራ መሆኑና በከተማው የሚገኙ የፖለቲካ አመራሮች ከደሞዛቸው ላይ እያንዳንዳቸው  አንድ ሺህ ብር ወጪ በማድረግ ለአንድ ግለሰብ ድጋፍ የማድረግ ሁኔታ መኖሩ፣
 • የኮቪድ -19 ወረርሽኙን ተከትሎ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች በከተማው የሚገኙ የእድር ምክር ቤቶች እያደረጉት ያሉት አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑና አስፈፃሚ አካላት ለዚህ ከፍተኛውን ድርሻ ፃጽ መቻላው፣

 

             ከታዩ የአሰራር ክፍተቶች ዋናዋናዎቹ

 

 • በከተማ አስተዳደሩ በመንግስት ትምህርት ቤቶች ለሚኖሩ ተማሪዎች ምገባ ሲያደርጉ የነበሩ እናቶች በኮቪድ-19 ምክንያት ትምህርት በመቋረጡ ስራቸውን በማቆማቸው የተፈጠረውን ከፍተኛ የሆነ ችግር ለመቅረፍ በየደረጃው ያለው የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ መዋቅር የተሰራው ስራ ከችግሩ ስፋት አንፃር በቂ አለመሆኑ፣ ይህም የተጠያቂነት አሰራር እንዳልተዘረጋ የሚያሳይ መሆኑ፣
 • በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በኩል በወረዳዎች ተደራጅተው ስራ ለማግኘት በጥረት ላይ የሚገኙ አካል ጉዳተኞችና አረጋዊያን ወደ ስራ ለማስገባት አለመቻልና ለብዙ ጊዜያት አረጋዊያንና አካልጉዳተኞች ሲኦሲ ምዘና አለመውሰዱ ምክንያት ወደ ስራ አትገቡም የሚል ምላሽ መሰጠቱና ለዚህም አማራጭ መንገዶችን በማዘጋጀት መፍትሄ ያለመስጠት መታየቱ፣
 • የኮረና ወረርሽኝ በአገራችን መከሰቱ በተሰማበት ወቅት ከፌደራል እስከ ወረዳ ባለው መዋቅር በጠቅላይ ሚኒስትሩ፣በከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎችና በታዋቂ ግለሰቦች በየመንደሩ እስካሉ ወጣቶች ሲሰጥ የነበረው የግንዛቤ የመፍጠር ሁኔታዎች በነበረው ግለት እየቀጠለ አለመሆኑና መቀዛቀዙ ለዚህም በመንግስት በኩል እተወሰደ ያለው እርምጃ አነስተኛ መሆኑና ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ ግንዛቤ ስራው የለም የሚባል ደረጃ መድረሱ፣
 • የግንዛቤ ማስጨበጫ በሚሰራበት ወቅት በተለያዩ ሚዲያዎች አማካኝነት የሚደረጉ ድጋፎች በመመልከት ህብረተሰቡ እያገኘ ካለው ድጋፍ ጋር በማነፃፀር በወረዳ ደረጃ ለኛ የመጣ ድጋፍን በላችሁት የሚል ቅሬታ እየፈጠረ መሆኑና በዚህም የተነሳ  ግልፅነትና ተጠያቂነት ባለው መልኩ ከመስራት አንፃር ክፍተት መኖሩ፣
 • በየወረዳው የደሀ ደሀ ናቸው በሚል የተመለመሉና ደረጃ የተሰጣቸው ለችግር የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ የሚሰጣቸው በቅደም ተከተል በመሆኑና የተደረገላቸው ድጋፍ መጠን ምንም ይሁን ምን በደረጃው መሰረት ድጋፉን ካገኙ የድጋፉን በቂነት ሳይቃኝ ሌሎች ያልተረዱ አካላት እስኪረዱ እንዲጠብቁ ሚደረግበት አሰራር በድጋሚ ድጋፍ ሊያገኙ የሚገባቸው ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፉን እንዳያገኙ የሚያደርግ ሂደት የግልፅነት፣ፍትሀዊነትና ርትዕነትና ሁሉን አቀፍ አገልግሎት ከመስጠት መርህ ክፍተት የፈጠረ መሆኑ በቁጥጥር ወቅት  የተለዩና ጉዳዩ አኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተፅዕኖ አንፃር  አስፈፃሚውና ሁሉም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የየድርሻቸውን ሚና በመጫወት ለተጋላጭ ወገኖች የሚደረገውን ድጋፍ አጠናክሮ በመቀጠልና ክፍተቶቹን በመድፈን ቫይረሱን ለመቆጣጣር የሚደረገውን ጥረት ስኬታማ በማድረግ የተጣለባቸውን ሀላፊነት እንዲወጡ ተቋሙ ጥሪውን ያቀርባል ፡፡