Asset Publisher Asset Publisher

ኮሚቴው፤ የሕዝብ እንባ ጠባቂ

ኮሚቴው፤ የሕዝብ እንባ ጠባቂ የዴሞክራሲ ኣርአያ እንዲሆን አሳሰበ።
በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በሌሎች ተቋማት ዴሞክራሲ እንዲጎለብት ኣርአያ መሆን እንዳለበት አሳሰበ፡፡
ቋሚ ኮሚቴው ማሳሰቢያውን የሰጠው፤ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋምን የ2014 በጀት ዓመት የአሥር ወራት የእቅድ አፈፃፀም በዛሬው ዕለት በገመገመበት ወቅት ነው፡፡
የሕግ፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ እፀገነት መንግሥቱ፤ በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲዘረጋ እና እንዲጎለብት የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ሚና ትልቅ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ተቋሙ በዘርፉ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፤ ራሱን መፈተሽም አለበት ብለዋል፡፡
የተከበሩ ሰብሳቢዋ አክለውም፤ ተቋሙ በሕግ የተሰጠውን ስልጣን ተጠቅሞ፣ ሕዝብ የሚጠብቀውን የተገልጋይነት ርካታ ማምጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
የተቋሙን አሠራር በማዘመንም ዜጎች በመልካም አስተዳደር እጦት የሚደርስባቸውን ችግር ለመቅረፍ መጣር እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
“ከመረጃ ፍሰት ጋር በተያያዘ ባለንበት ወቅት የሚስተዋለውን የተዛባ የመረጃ ስርጭት ችግር ለመፍታት አዋጅ ማውጣት አስፈላጊ ቢሆንም፤ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አሁን ያለውን አዋጅ በአግባቡ ተጠቅሞ፣ አዋጁ እስኪሻሻል ድረስ በመረጃ ነፃነት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አለበት፡፡ በመገናኛ ብዙኃናት ሲጠየቁ መረጃ የማይሰጡ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ አዋጁን መሠረት አድርጎ መሥራት ይኖርበታል” የተከበሩ ወ/ሮ እፀገነት እንዳሉት፡፡ አስተዳደራዊ በደል ደርሶብኛል ብለው የሚመጡ አካላትን በማስተናገድ፤ የዜጎችን እንባ ማበስ እንዳለበትም ጠቁመዋል-የተከበሩ ሰብሳቢዋ፡፡
የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም፤ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቄያቸው እንዲመለሱ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበው፤ ዜጎች ወደ ቀድሞ ሕይወታቸው እስኪመለሱ ድረስ ሁሉም አካላት እንዲተባበሩ የተከበሩ ወ/ሮ እፀገነት መንግሥቱ ጠቁመዋል፡፡
የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እንባ ጠባቂ ክቡር እንዳለ ኃይሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ተቋሙ በባለሙያዎቹ አማካኝነት በሌሎች ተቋማት ቁጥጥር ካደረገ በኋላ፣ የመውጫ ስብሰባ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ ተቋማቱ በቀጣዩ ቁጥጥር ‘አለባችሁ’ የተባሉትን ችግር በአሳማኝ ምክኒያት ካልፈቱ ተቀብለው እንደሚያልፉት እና ያልፈቱት ያለምክኒያት ከሆነ ደግሞ እንዲያስተካክሉ ስለሚደረግ፤ ከተቋማት ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡
ዋና እንባ ጠባቂው አክለውም፤ የመልካም አስተዳደር ችግር ካልተፈታ የሚጎዳው መንግሥትን በመሆኑ፣ መንግሥት የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግር የሚፈጥሩ አካላትን ተጠያቂ ከማድረግ አንጻር የተቋሙ ክፍተት በመሆኑ፤ አሠራራቸውን እንደሚያስተካክሉ አብራርተዋል፡፡
በተመሳሳይም መረጃ የሚከለክሉ አካላትን በመገናኛ ብዙኃን ማጋለጥ እንደሚቻል እና ለሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ይግባኝ ማቅረብ እንደሚችሉ በአዋጁ ቢደነገግም፤ ከመገናኛ ብዙኃን ተቋማት የሚያጋልጡ አካላት አለመኖራቸውን እና ባለፉት ዓመታት ይግባኝ የጠየቁ የመገናኛ ብዙኃን ሦስት ብቻ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የመገናኛ ብዙኃን እና የመረጃ ነጻነት አዋጅ፤ አዋጅ ቁጥር ፭፻፺/፪ ሺህ ዓ.ም ሆኖ ከወጣ በኋላ፣ ላለፉት 14 ዓመታት እንዳገለገለ እና አሁንም እየተሠራበት
እንደሆነ ይታወቃል፡፡